
ለአገልግሎት ጥራት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ወደ ሥራ በመገባቱ የተሻለ ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ማስቻሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሃብቴ ገ/ሚካኤል በዚህ ጊዜ እንዳሉት፦ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለአገልግሎት ጥራት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ወደ ሥራ በመገባቱ የተሻለ ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ አስችሏል።
በጥናት በተገኙ ግኝቶች ላይ በመመስረት አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ላይ ስሰሩ ቆይተዋል ነው ያሉት አቶ ሃብቴ፡፡
የባላሙያዎችን አቅም መገንባት፣ ተቋማትን በመድሃንቶችና በሌሎች የህክምና ግብዓቶች ማደረጀት፣ የስና ምግባር ችግሮችን ማረምና የባለሙያዎችን የደሞዝ የድዩቲና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን መመለስ እንዲሁም ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ክትትል ማድረግ በዓመቱ ከተሰሩ ሥራዎች የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
ተከታተይ የሆነ የምክክር መድረክ በጤና ተቋማት፣ በማህበረሰቡና በባለሙያዎች መካከል እንዲካሄድ ማድረግና የቦርድ አመራሮች ወደ ተቋማት ጠጋ ብለዉ ችግሮችን እየፈቱ እንድሄዱ የተሰራበት መንገድም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንደነበረዉ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሃብቴ፦ በጤና ተቋማት ዉስጥ የመድሐኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ ያለመኖር ህብረተሰቡ በተለያዩ አጋጠሚዎች ስያነሳቸዉ የነበሩ ችግሮች እንደመሆናቸዉ መጠን ችግሩን ለማረምም በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል።
በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች አማካይነት ከሚቀርቡ የህክምና ግብዓቶች በተጨማሪ ህብረተሰቡን በስፋት በማሳተፍ ተቋማት በቂ ግብዓት እንድኖራቸዉ የተሰራበት ዓመት ነዉ ያሉት አቶ ሃብቴ።
በዚህም፦ ከ3 መቶ 80 ሚልየን ብር በላይ ግምት ያለቸዉ የተለያዩ መድሐኒቶችና የህክምና ግብኛቶች እንድቀርቡ ተደርጓል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በክልሉ ዉስጥ ግንባታቸዉ ተጠናቆ አገልግሎት ለሚጀምሩ በተለያየ ደረጃ ለምገኙ ተቋማት በክልሉ መንግስት በተደረገ ከ11 ሚልዮን ብር በላይ የባጀት ድጋፍ መድሐኒቶች እየቀረቡ አገልግሎት እንዲጀምሩ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩንም የቢሮዉ ምክትል ኃላፊ አንስተዋል፡፡
ሞዴል የማህበረሰብ መድሐኒት ቤቶችን ማስፋፋት፣ ለኦዲትና ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ የሆኑ መድሐኒት ቤቶችን ከማሳደግ አንጻር የተሰሩ ስኬታማ ተግባራት መኖራቸውንም አውስተዋል።
አቶ ሃብቴ፦ በበጀት ዓመቱ ዉስጥ ብቻ 11 ሞዴል የማህበረሰብ መድሐኒት ቤቶችንና 11 ለኦዲትና ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ የሆኑ መድሐኒት ቤቶችን ስራ በማስጀመር አገልግሎት መስጠት እንድችሉ ተደርጓል፡፡
የማህበረሰቡን ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በዓመቱ ዉስጥ የማአጤመ ተጠቃሚ አባለት ምጣኔ ከማሰደግ አንፃር ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በተደረገ ርብርብ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ አባ/እማዎራዎችን አባል በማድረግ በጠቅላለዉ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
አባል ከሆኑ ሕብረተሰብ ክፍሎች ከ6 መቶ 22 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰበሰብ ወደ ባንክ ገቢ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ይህም ለጤናዉ ሴክተር የፈይናንስ ቀጣይነትን ከማረጋገጥ አንፃር ወሳኝ ሚና ያለዉ ነዉ በማለት የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም አብራርተዋል ኃላፊው።
ከፍተኛ ቋት በመመስረትና የቁርጥ ክፍያ ስርዓትን በመተግበር ፕሮግራሙን ዉጤታማ ለማድረግ የተሰራዉ አበረታች ሥራ ክልላችንን በሀገር ደረጃም ልምድ የሚቀሰምበትና የተሞክሮ ማዕከል እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።
ደም ለሚያስፈልጋቸዉ ታካሚዎች በበቂ ሁኔታ ደም ለማቅረብ የሚያስችል ስራ በቡታጅራና ሆሳዕና ደም ባንኮች ዉስጥ የተሰራበት ስራም እጅግ አበረታችና ዉጤት ያመጣበት እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በቀጀት ዓመቱ ዉስጥ 15 ሺህ 4 መቶ 31 ዩኒት ደም ለማሰበሰብ ታቅዶ 14 ሺህ 1 መቶ 78 ዩኒት ደም በማሰበሰብ የዕቅዱን 91.8% በመፈጸም የክልሉን ጤና ተቋማት የደም ፍላጎት ሙሉ በሙሉ መሸፈን የተቻለበት እንደሆነ የዘርፉ ኃላፊ አንስተዋል።
በዚህም፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰሩ አበረታች ስራዎችን በማስቀጠል በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስገኘት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አረጋግጠዋል።
በአብርሃም ሙጎሮ