ለውጤታማ የጤና ተግባራት አፈፃፀም ለዘርፉ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠትና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሚፈጠሩ ውስንነቶች ተጠያቂነትን በማስፈን የጤናውን ዘርፍ ብልፅግና ማሣደግ እንደሚገባ ተገለፀ

  • Post last modified:October 4, 2025

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ዓመታዊ የጤና ጉባዔውን እያካሔደ ሲሆን በጉባዔው ላይ የ2017 በጀት ዓመት የጤና ሴክተር ዕቅድ አፈፃፀም ለጉባዔው ተሣታፊዎች ቀርቧል።

በሪፖርቱ እንደተመላከተው ከሆነ፤ የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በማነቃቃት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤት መምጣቱ ተጠቁሟል።

በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት፣ በቅድመ ወሊድ አገልግሎት፣ ነፍሰ ጡር እና ወላድ እናቶች ማቆያ አዘጋጅቶ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት በ2017 የተሻለ እና እያደገ የመጣ አፈፃፀም የተመዘገበ ሲሆን በተለይ በሰለጠኑ የማዋለድ ባለሙያዎች ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠው አገልግሎት በቀጣይ በላቀ ደረጃ መሻሻል እንደሚገባው ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።

የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል ረገድ የጎርፍ አደጋ፣ የወባ፣ የኩፍኝና የኮሌራ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ያላሰለሰ ጥረት በክልሉ አጥጋቢ ውጤት የተገኘበት እንደነበረ ሪፖርቱ አመላክቷል።

የጤና ስርዓት ቁጥጥርን በተመለከተ በጤና ተቋማት ቁጥጥር እና እድሳት የሚታይ ለውጥ የመጣ ቢሆንም በቀጣይ በላቀ ትኩረት ሊሠራበት ይገባል ተብሏል።

ጉባዔው በሁለተኛ ቀኑ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለ2018 በጀት ዓመት ከሁሉም መዋቅሮች ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ርክክብ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እና ተቋማት ለተሻለ አፈጻፀም የሚያነሳሳ ሽልማትና ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።

ደሬቴድ