
(መስከረም 23/2018) ”በባለቤትነት ላይ የተመሰረተ እውቅናና ተጠያቂነት ለጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል የክልሉ ጤና ቢሮ አመታዊ የጤና ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደተናገሩት ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የጤና ስርዓቱን ማዘመን ይገባል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በሴክተሩ የነበሩ መሰረታዊ ተግዳሮቶችን በመለየት በተሰሩ ስራዎች ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት ኃላፊዉ በዓመቱ በጤናው ሴክተር ሞዴል የሆኑ በርካታ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ በበጀት ዓመቱ የጤና ቁጥጥር ስርዓቱን ለማሻሻል በተሰራው ስራ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጨና በመቀነስ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
የጤናው ስራ ተግባቦትን ይጠይቃል ያሉት አቶ ሳሙኤል ለዘርፉ ውጤታማነት ሁለንተናዊ ቅንጅትና ትብብር ብሎም አመራር ሰጪነት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
የእናቶችና ህፃናት ጤና ሁኔታን ለማሻሻል ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልፀው የመድኃኒትና ህክምና ግብአት አቅርቦት፣ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶቾ ግንባታና አገልግሎት ላይ በተከናወኑ ተግባራትም ተጨባጭ ውጤትን ለመምጣት ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይ የጤና ስርዓት ግንባታ ማጠናከር፣ የማህበረሰቡን የጤና ባለቤትነትና ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ የማበረታቻና የተጠያቂነት አሰራር ስርዓትን መዘርጋት፣ የአፈፃፀም ውጤታማነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደገለፁት የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓትን ለማጠናከር በቢሮው ቀደም ሲል በርካታ ስራዎች መሰራቱን ገልፀዋል።
ተግባራትን በኃላፊነት በመተግበር የጤናውን ስርዓት በማዘመን ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መስራት ያስፈልጋል ብለው በቀጣይ ደካማና ጠንካራ ጎኖችን በመለየት በጤናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዛሬው ሰነድ ቀርቦ የቡድን ውይይት በማድረግ ለቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ይይዛል ተብሎ ይጠብቃል።
በመድረኩም የክልል፣ የዞን፣ ልዩ ወረዳና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ኃላፊዎች ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።