
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል በጤናው ዘርፍ አየተከናወኑ ያሉ ተግባራቶች ለውጥ አምጪ እና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና አገ/ት በፍታሀዊነትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራቶች በማገዝ ረገድ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አይተኬ ሚናቸውን መጫወታቸውንም ገልጸዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንደ ሀገር በተለያየ ጊዜ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ድንገተኛ ወረርሽኞች በማህበረሰቡ ላይ የከፋ የጤና ጉዳት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከማስከተላቸው በፊት ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅናም ሰተዋል።
የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎት እና የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ተግባራትን መፈጸም ይገባል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ በሀገራችን ከ16 ሺህ በላይ ጤና ኬላዎች መኖራቸውን በመግለጽ ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር የመጀመሪያ ጤና ክብካቤን ማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
በመንግስት በኩል የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን በጥራት በብዛት በማሰልጠንና በማሰመራት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
በቀጣይም ዘርፉን ለማሻሻል በሚቀጥሉት ዓመታትም አዲስ የተቀረፀውን የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ-ካርታ ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የማሕበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት እና የጤና ባለሙያዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ባስተላለፉት መልዕክት የዜጎችን የጤና ተጠቃሚነት ለማሻሻልና ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አገልግሎቶችን ማስፋፋት እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በክልሉ በመጀመሪያ አሀድ በሀገር ተሸላሚ የሆነ ወረዳ ያለበት ፣በኮምፕሬንሲቪ እና በጠቅላላ ሆስፒታሎች እንዲሁም ተወዳዳሪ ተቋማትና ወረዳዎችን ከመፍጠር አንፃር ተወዳዳሪ ክልል መሆኑን ጠቅሰዋል ።
የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጤና ክብካቤ አገልግሎትን ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
መከላከልን መሠረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመተግበር የእናቶችን እና የህጻናት ሞትን ለመቀነስ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በሌሎች በጤናው ዘርፍ በሚከናወኑ ተግባራቶች ውጤታማ ለውጥ አምጪ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሆነም አቶ ሳሙኤል አክለው ገልጸዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጤናውን ሴክተር ተግባር በአግባቡ ለማሳለጥ አጋዥ ከመሆኑ ባሻገር የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ከሚያጋጥሙት ውስብስብ የጤና ችግሮች እንዲላቀቅ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ባለሙያዎቹ እያበረከቱት ላለው ከፍተኛ አስታዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማሕበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ፣ ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ