
(ሆሳዕና ግንቦት 6/2017) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባትና የጤና ዘመቻ ክልል አቀፍ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀላባ ዞን አስጀምሯል።
በክልሉ ከግንቦት 6 እስከ 15/2017 የሚካሄደው ክልል አቀፍ የኩፍኝ ክትባትና የጤና ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ኡዳና ጤና ጣቢያ ተካሂዷል።
መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንደገለፁት በክልሉ መከላከል መሠረት ባደረገ የጤና ስርዓት የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በተለያዩ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋና ሌሎች ምክንያቶች ክትባት የማይወስዱና የሚያቋርጡ ህፃናት በመኖራቸው የተቀናጀ ክትባት ዘመቻ መስጠት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር 17 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚጠጉ ህፃናት የኩፍኝ በሽታ ክትባት እንደሚሰጥ ገልፀው በክልሉ 1 ሚሊየን 19 ሺህ 611 ለሚሆኑ ህፃናት በጤና ተቋማትና በጊዜያዊ ክትባት መስጫ ጣቢያዎች ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት እድሜያቸው ከ9 ወር እስከ 5 ዓመት ለሆኑ ህፃናት የሚሰጥ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
በተቀናጀ ክትባት ዘመቻው የኩፍኝ ክትባት፣ ሌሎች የመደበኛ ክትባቶች ያልጀመሩና ያቋረጡ ካሉ፣ የምግብ እጥረት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ መስጠት፣የፌስቱላ እና የማህጸን ውልቃት ችግር ያለባቸው እናቶች ልየታ፣ የታመሙ ህጻናትን የመለየት፣ የአንጀት ትላትል መድሃኒት እደላና መሰል አገልግሎቶች እንደሚሰጥም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
ክትባት ማስከተብ የህፃናትን ህመምና ሞት እንዲሁም የአካል ጉዳት ለመቀነስ የጎላ ፋይዳ እንዳለዉ ገልፀው የሚሰጠውን ክትባት በተገቢው መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዘመቻው ስኬታማነት የሚዲያ አካላት ፣የሃይማኖት አባቶችና በየደረጃው ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
የቢሮዉ የእናቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች ጤናና ሥርዓተ ምግብ አገልግሎቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሌጂሶ በክልሉ ለክትባት ዘመቻው የልየታ ፣ የግብዓት አቅርቦትና ከአጋር አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በተለያዩ ሰው ሰራሽ በተፈጥሮ እና ኮቪድ ምክንያት በሀገራችን ከ5.2 ሚሊየን በላይ ህፃናት ለኩፍኝ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን በጥናት መረጋገጡን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
የኩፍኝ በሽታ ተላላፊ በመሆኑ መደበኛ ክትባት በማጠናከርና በዘመቻ የህፃና በሽታን የመከላከል አቅምን የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች በተመሳሳይ የክትባት ዘመቻው መሰጠት መጀመሩን ገልፀው በየቀኑ በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።
የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ዶ/ር ሸምሰዲን ረሺድ የህፃና በሽታን በክትባት መከላከል እየተቻለ ለበርካታ ህፃና ሞት ምክንያት መሆኑን ገልፀው በዘመቻው በሀላባ ዞንም ከ64 ሺ በላይ ህፃናት የሚከተቡ መሆኑን ተናግረዋል ።
በመጨረሻም የጤና ጣቢያ ጉብኝትና የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተቋሙ አከናውነዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የክልልና የዞን የወረዳ አመራሮች ባለሞያዎች የአጋር ድርጅት ተወካዮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በኤልያስ ቲርካሶ