
የቢሮው የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግመገማ እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ አየተካሄደ ነው ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃልፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ባስተላለፉት መልዕክት በበጀት አመቱ ኤች አይቪ ኤድስን የመከላከል እና መቆጣጠር ስራዎች በትኩረት መሰራታቸውን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የምርመራ እና ጥምር የሆኑ የኤች አይቪ መከላከል እና መቆጣጠር ተግባራት ውጤት አምጪ ናቸውም ብለዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ተግባርን ለማጠናከር የክልሉ የፊት አመራሮች በተገኙበት የተደረገው የንቅናቄ መድረክ በህረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠሩን የጠቆሙት አቶ አሸናፊ በዚህ መድረክ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የኤችአይቪን ጉዳይ በባለቤትነት በመያዛቸው አበረታች ውጤቶች ስለመታየታቸው ተናግረዋል።
የባህሪ ለውጥ እና የተግባቦት፣ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እንዲሁም የኤች አይቪ የላቦራቶሪ ምርመራ ጥራትን ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ አምጪ መሆናቸውንም አቶ አሸናፊ አክለው ገልጸዋል።
እንደ ሀገር በ2030 ኤች አይቪ ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ መዘናጋቶች ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አቶ አሸናፊ ጥሪ አቅርበዋል።
በቢሮው የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው የኤች አይቪ ስርጭትንና በኤድስ ምክንያት የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለማስቀረት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ውሳኔ ሰጪ አካላት የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጠየቁት አቶ አለማየሁ ኤች አይቪ ኤድስ በዜጎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የከፋ የጤና ጉዳት ማህበራዊና ኢኮኖያዊ ቀውሶችን ለማስቀረት የአመራሩና የፈጻሚው ቁርጠኝነት አየጎለበተ እና እየተሻሻለ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዝናሽ ደለለኝ