
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፦ በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል።
አቶ አሸናፊ፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ መፈታት ያለባቸውን ዋና ዋና የጤና ጉዳዮችን በመለየት ወደ ሥራ ተገብቷል።
በዚህም፦ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማጠናከር፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመንና በጤና ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመፍታት በእቅድ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል አቶ አሸናፊ።
ተቀዛቅዞ የነበረውን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በአዲስ መልክ ወደ ሥራ ለማስገባት የአቅም ግንባታ ሥልጠናና ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረኮች የክልሉ የፊት አመራሮችና የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተደርጓል ነው ያሉት ኃላፊው።
በዚህም፦ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተተክለው ከመሥራት አኳያ ክፍተት መኖሩ በጥናት ተለይቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲወስዱ በመደረጉ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል ሲሉም ተደምጠዋል።
አቶ አሸናፊ፦ መሠረተ ልማት ከማሻሻል አንጻር በበጀት ዓመቱ 17 አጠቃላይ ጤና ኬላ ግንባታ አስጀምረናል፤ በዚህም ህብረተሰብን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ ተሞክሯል።
ከዚህም 5 አጠቃላይ ጤና ኬላዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፤ የተቀሩትን በጊዜ ሂደት በማጠናቀቅ የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል አቶ አሸናፊ።
አቶ አሸናፊ፦ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ በ26 ወረዳዎች ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት በሰራተኞች ዘንድ ከፍተኛ የስራ መነቃቃትና ተነሳሽነት እንዲፈጠር ተደርጓል።
በበጀት ዓመቱ የጤና ኤክስቴንሽን የደረጃ ዕድገት፣የዝውውር እና ማትጊያ መመሪያ መዘጋጀቱ ፣የፖሊዮ እና የተቀናጀ ኩፍኝ ዘመቻዎች አፈፃፀም ማደጉ፣ከ39 ሺህ የሴቶች ልማት ህብረት ጋር በመቀናጀት የጤና ኤከስቴንሽን ስራው እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው ጠቁመዋል፡፡
አቶ አሸናፊ፦ በስምንት ወረዳዎች ላይ የፅዱ ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ ተጀምሮ ህብረተሰቡ ከተላላፊ በሽታዎች ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ዕድል ተፈጥሯል።
በዚህም፦ 514 የመንገድ ዳር መፀዳጃ ቤት በመስራት 108 ቀበሌዎች ሜዳ ላይ ከመጸዳዳት ነፃ ሆነው በመመረቁ በአጠቃላይ ሜዳ ላይ ከመጸዳዳት ነፃ የሆኑ ቀበሌዎች ብዛት 613 / 54 በመቶ/ ሽፋን መድረሱን አቶ አሸናፊ አንስተዋል ።
በጤና ተቋማት የነብሰ ጡር እናቶች ማቆያ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ እና የወሊድ አገልግሎትን በማሻሻል የእናቶችን እና የጨቅላ ህጻናት ህመምና ሞት መቀነስ መቻሉን አቶ አሸናፊ አክለዋል።
አቶ አሸናፊ፦ በበጀት ዓመቱ 40 ሺህ ህፃናት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከተቡ እና 21 ሺህ ህጻናት ክትባት ጀምረዉ ያቋረጡትን ፈልጎ በመለየት በቂ የክትባት አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓልም ብለዋል
በክልሉ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ተላላፊ የሆኑ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ መጠነ ሰፊ ስራ በመሰራቱ በሽታዎቹን መቀነስ ተችሏል ።
አጠቃላይ በዘርፉ የተገኙት ውጤቶችን ሀላፊዉ ሲያብራሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተተክለው እየሰሩ መሆኑ፣ ህብረተሰቡ በጤና ስራ ላይ ባለቤት እየሆነ መምጣቱ እና የእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነስ መቻሉ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል
በዘርፉ እንደምርጥ ተሞክሮ የተወሰደው 153 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በህብረተሰብ ተሳትፎ የጤና ኬላ ግንባታ መከናወኑ እና በጤና ኤክስቴንሽን የሴቶች ህብረት ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑ የ2017 የዘርፉ አፈፃፀም አበረታች ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ማሳያ ነዉ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት የተገኙ ዉጤቶችን በማስቀጠልና በ2018 በጀት ዓመት ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት ይገባልም ብለዋል አቶ አሸናፊ።
በሸምሲያ አደም