በበጀት ዓመቱ የሕብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል ፦ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

  • Post last modified:August 13, 2025

በበጀት ዓመቱ የሕብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት፦ በበጀት ዓመቱ የሕብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርቷል ብለዋል ።

በክልሉ ጤና ቢሮ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውጤታማ የድንገተኛ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት መፈፀም መቻሉንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አቶ ማሙሽ፦ በ2017 በጀት ዓመት የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ተግባራት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በምላሽና መልሶ በማገገም ተግባራት ረገድ ውጤታማ ስራዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በዚህም፦ መጀመሪያ ይከሰታሉ ተብለው ከተለዩ ዋና ዋና ድንገተኛ የጤና ችግሮች መካከል ወባ፣ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ኤምፖክስ ፤ የጎርፍ አደጋ፣ የተወሳሰበ የምግብ እጥረት ችግር፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሚደርስ የሰዎች መፈናቀልን እና ተያያዥ ጉዳቶች በመለየት ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ለተከሰቱ ድንገተኛ የጤና ችግሮች በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመተባበር በማህበረሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አስቀድሞ በመተንበይ፣ የቅኝት ስራዎችን በመስራት፣ በሰው ኃይል እና በግብዓት ረገድም በቂ ዝግጅት በማድረግ በሰውና በንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ፈጣን ምላሽ መስጠት መቻሉን አውስተዋል፡፡

በተለይም የወባ ወረርሽኝን ለመከላለከልና ለመቆጣጠር በተቀናጀ የሪፖርት ቅብብሎሽ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በሚመራ ክልላዊ የድንገተኛ ጤና አደጋዎች መከላከል ግብረ ሃይል ግምገማ በማድረግ የተለያዩ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ስልቶች እና አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ክትትል ተደርጓል ሲሉም ተደምጠዋል አቶ ማሙሽ።

በክትትሉም የወባ ወረርሽኝ ከመቀነስ አኳያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው የበልግ ዝናብ ተከትሎ የመጨመር አዝማሚያ ያሳየው የወባ ጫና ለመቆጣጠር የንቅናቄ ሰነድ እና የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ዝግጁነትና ምላሽ እቅድ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ጤና መዋቅር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የድጋፍና ክትትል ተግባራት በመተግበር የስርጭት ጫናው መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል

የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ከመስከረም ወር ጀምሮ ሊከሰት የሚችለው ከፍተኛ የወባ ስርጭት ወቅት(major transmission season) አስመልክቶ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለሁሉም መዋቅሮች በማድረስ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በገለጻቸው አውስተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የኮሌራ ወረርሽኝ በሁለት ወረዳዎች ብቻ ሶስት ታማሚዎች መገኘታቸውን እና ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የታየበት ዓመት እንደነበር አንስተው በተለይም በክልሉ ከሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከዞኖችና ከልዩ ወረዳዎች የጋራ የውይይት መድረክ በማካሄድ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ማህበረሰቡን የማንቃት ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

በቀጣይም የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የኮሌራ ወረርሽን አስመልከቶ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተጽፎ የጥንቀቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን እንደክልል ለቅድመ ዝግጅት የሚሆን ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት መሰረታዊ መድሃኒት ግዢ በመፈጸም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የኩፍኝ ወረርሽኝ በተመለከተ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በተገበሩ የጠናከረ ሰርቬላንስ ፤ መጠነ ሰፊ የክትባት ተደራሽነት እና ጥራት ተግባራት ከ2016 በጀት ዓመት አንጻር ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ በሚባል መልኩ መቀነሱን የገለጹ ሲሆን ወረርሽኙ በአሁን ሰዓት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የድንገተኛ ጤና አደጋዎች በቴክሎኖለጂ ከማስደገፍ አንጻር የPHEM-DHIS2 የመረጃ ቋት ስርዓት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች መተግበሩን ገልጸው መረጃዎች በሚጠበቀው ፍጥነት እና ጥራት በመሰብሰብ ለውሳኔ የማዋል ተግባር መጀመሩን አውስተዋል፡፡

አቶ ማሙሽ፦ በክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ በ2017 በጀት ዓመት ለህብረተሰቡ የምርመራ አገልግሎት ለመስጠት በጂን ኤክስፔርት ማሽን ማዕከላት፤ የዲያግኖስቲክ አገልግሎቶች መካከል የጫቅላ ህጻናት የኤች አይ ቪ መጋለጥ ቅድመ ምርመራ፤ የኤች.አይ.ቪ ቫይራል መጠን ምርመራ፤ የማህጻን ጫፍ ካንሰር ቫይረስ መጠነ ምርመራ፤ (Human Papilloma Virus ናሙና፤ የጉበት በሽታ አምጪ ቫይረስ መጠነ ምርመራ፤ Heatitua B and C Viral Load ናሙና፤ የኩፍኝና የሩቤላ ምርመራ ናሙና፤ የአጠቃላይ ማይክሮባዮሎጂና ምርመራ እና የመድኃኒት ፊቱንነት ምርመራ የናሙና ቅብብሎሽ ሰንሰለት ኔትውክን በመጠቀም ለህሙማን የምርመራ አገልግሎት ተሰጥተዋል፡፡

የባክተሪዮሎጂካል ካልቸር ምርመራ
ከተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች የሚወሰዱ ናሙናዎችን በመቀበል (የባክቴሪዮሎጂካል ካልቸር ምርመራና የመድኃኒት ፊቱንነት አገልግሎት) ለመስጠትና እንዲሁም በሽታ አምጭ የሆኑ ተህዋሲያን ለመለየት የአይነ ምድር ናሙና፤ የዉሃ ሽንት ናሙና፣ የደም ናሙና፣ የአከርካሪ ዉስጥ ፈሳሽ ናሙና፤ የብልት ፈሳሽ ናሙና፣ ለተለዩባቸዉ ናሙናዎች የመድሃኒት ፍቱንነት (AST) ምርመራ በመስራት ህመምተኞች ለህመማቸዉ ተገቢውንና ትክክለኛ ህክምና እድያገኙ በታቀደዉ መሠረት ወደ ተቋሙ ለመጡ ህሙማን በሆሳዕና ቅርንጫፍ ላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡

የኮሌራ እና መጠጥ ዉሃ ጥራት ምርመራ
የኮሌራ ወረርሽኝ ከተጠረጠረባቸው መዋቅሮች የኮሌራ ምርመራ ናሙናዎች በመውሰድ የካልቸርና ሴሮሎጂካል ምርመራ ተደርጎ የኮሌራ ተህዋስያንን መለየት ተችሏል፡፡

ከነዚህ መዋቅሮች ማለትም ከዞን፤ ከወረደ፤ ከከተሞች እንዲሁም ከገጠር ቀበሌዎች የሚሰራጫዉ የመጠጥ ዉሃ ለመጠጥ አገልግሎት መዋል የሚችል ወይንም የተበከለ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚደረግ የመጠጥ ዉሃ ምርመራ ዓይነት ሲሆን በበጀት ዓመቱ የኮሌራ ወረርሽኝ ክስተት ከተጠረጠረባቸው መዋቅሮች ከማጠራቀሚያዎች፤ የውሃ ምንጮችና የውሃ መያዣዎች ላይ የውሃ ናሙናዎችን በመሰብሰብ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡

አቶ ማሙሽ፦ በክልላችን 54 Gene Xpert ማሽኖች በ 52 ጤና ተቋማት ውስጥ የሪፋምፒስሊን መድኃኒት የተላመደ MDR-TB ምርመራ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ወደ ሐዋሳ እና ወደ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ የሚላከዉ የመድኃኒት የተላመደ ቲቢ (MDR-TB) ህሙማን ልየታ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የGene Xpert MTB/RIF ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማት በጥር ወር 40,000 ናሙናዎችን ለመስራት የታቀደ ሲሆን 45,415 (›100%) መስራት ተችሏል፡፡

ከነዚህም ሃያ ዘጠኝ የሪፋምፒስሊን መድኃኒት የተላመደ MDR-TB፤ 2,714 በመደበኛዉ የቲቢ ህክምና መዳን የሚችል ቲቢ የተገኘ ሲሆን ቀሪ 42,675 (93%) የሚሆኑት የትኛዉም ዓይነት ቲቢ ያልተገኘባቸዉ ሲሆን 3088 የሚሆኑት ያልተፈለገ ዉጤት (Error, Invalid and No Result) ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የጨቅላ ህጻናት ከ18 ወር በታች የኤች አይ ቪ ምርመራ (Early Infant Diagnosis/EID) ኤች አይ ቪ ቨይረስ በደማቸዉ ዉስጥ ከሚገኝባቸዉ እናቶች የሚወለዱ ህጻናት በቨይረሱ መያዝ ያለያዛቸው ለማረጋገጥ እንዲሁም ህጻናቶቹ ተገቢ መከላከያና ህክም ለማስጀመር ያመች ዘንድ የሚደረግ ምርመራ ሲሆን በ2017 በኮንቬንሽናል ቫይራል ሎድ ማሽን (ምርመራ በክልሉ ላቦራቶሪ ለ 47 እንዲሁም በጂን ኤክስፕርት ማሽን ባለባቸዉ 15 ጤና ተቋማት ላይ ለ157 ህጻናት በድምሩ ለ 204 ህጻናት ምርመራ የተደረገ ሲሆን 6 (3%) ህጻናት ቫይረሱ ሲገኝባቸው ቀሪ 196 ህጻናት ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ታውቋል፡፡

ከክልላችን የኤች አይ ቪ መድሃኒት ህክምና ከሚከታተሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ መጠናቸውን ለመለካት አዲስ ተመርቆ ወደ ሥራ በገባው በክልሉ ላቦራቶሪ 2758 ናሙናዎች ሲመረመሩ ቀሪዎቹ በሐዋሳ፤ በአዲስ አበባ እና በጂማ ሜዲካል ኮሌጅ ላቦራቶሮዎች ናሙናዎችን በመሰብሰብና በማሸግና በመላክ ምርመራ ተደርጓል።

የወባ ተቋማዊ ምልከታ እና ሜንተርሺፕ(Malaria OSE and Mentorship)
በበጀት ዓመቱ በመልሶ ምልከታ የሚሳተፉትንና የውጤት ልዩነት ያለባቸውን ጤና ተቋማት ጨምሮ ሌሎች በመልሶ ምልከታ የማይሳተፉን ጤና ተቋማት በተቋሙ ላይ በሚደረግ መልሶ ምልከታ እና በሜንተርሺፕ ተደራሽ ይደረጋሉ ተብሎ የታቀዱትን በሙሉ ከፕሮጋርም ክፍሎች ጋር ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡

‎የክልሉን የጤና ስርዓት ለማጠናከር በአመቱ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን በተለይ በጤና ስርዓት ግንባታ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤታማነት ላይ፣ የክልሉ ሴቶች ልማት ህብረት በጤና ተግባር ላይ ያላቸው ተሳትፎ፣ በክልሉ ያሉ የወባ ዝርያ አይነት ልየታ ላይ፣ በአእምሮ ጤና ላይ፣ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በመሳሰሉት የጥናት ርዕሶችን የምርምር ስራ ተከናውኗል።

በሂደቱም በክልሉ እና ከክልል ውጪ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች እና ሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር ጠንካራ ቅንጅት መፍጠር ተችሏል።

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ለ2018 በጀት ዓመት የድንገተኛ ጤና አደጋዎች የመከላከልና የመቆጣጠር፣ የላቦራቶሪ አገልግሎትና የጤና ሪሰርች ተግባር ከምንጊዜም በተሻለ መልኩ ለመፈጸም ቅድመ ዘግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ በገለጻቸው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ማሙሽ፦ በክልሉ ጤና ቢሮ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተሰሩ ውጤታማ ሥራዎች የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የቢሮው አጠቃላይ ማኔጅሜንትንና ሠራተኞችን፣ የክልሉን መንግሥት፣ አጋር አካላትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።

በአብርሃም ሙጎሮ