
ቢሮው በበጀት ዓመቱ በተቀናጀ ዘመቻ የተከናወኑ ተግባሮች ግምገማና እውቅና የመስጠት መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንዳሉት፦ በተቀናጀ ጤና ዘመቻ በተሰሩ ሥራዎች የሚታይ ለውጥ ተመዝግቧል።
አቶ አሸናፊ፦ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከተቡ ህጻናትን በመለየት በቂ የክትባት አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓል።
በዚህ ሂደት 2 መቶ 36 ሺህ 3 መቶ 85 የነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች ልየታ ተደርጎ የምግብ እጥረት ያለባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠሩን አክለዋል አቶ አሸናፊ።
ከ5 ዓመት በታች ያሉ 1 ሚሊዮን 1 መቶ 68 ሺህ 6 መቶ 59 ህጻናትን በመለየት የምግብና ህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓል ነው ያሉት ኃላፊው።
በተጨማሪ 1 ሺህ 6 መቶ 51 የታመሙ ህጻናትን በመለየት ከጤና ተቋማት ጋር በማገናኘት ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እድል ተፈጥሯል ሲሉም ተደምጠዋል አቶ አሸናፊ።
አቶ አሸናፊ፦ በበጀት ዓመቱ በተሰሩ የጤና ዘመቻዎች ላይ የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው፦ በድጋፋዊ ክትትል ሥራዎች የተቀናጁ የጤና ዘመቻዎች በጥንካሬ የተሰሩ ናቸው ብለዋል።
አቶ ማሙሽ፦ በበጀት ዓመቱ በነበረው ጤና ዘመቻዎች የመገናኛ ሚዲያዎች የጎላ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው እውቅናና ምስጋና አቅርበዋል።
በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ጤና መምሪያዎች፣ ጽ/ቤቶች፣ መድኃኒት አቅራቢዎችና አጋር አካላት የእውቅና ሰርትፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ መጠነ ሰፊ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ ሲያካሄድ ቆይቷል። የኩፍኝ ክትባት፣ የካችአፕ ክትባት፣ የሥርዓተ ምግብ፣ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎቶችና የቤት ለቤት የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎች ተደርጓል።
በአብርሃም ሙጎሮ