በከምባታ ዞን የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በይፋ ተጀመረ

  • Post last modified:May 19, 2025

ግንቦት 6/2017 ዓ.ም በዞኑ ዕድሜያቸው ከ9-59 መካከል ለሚገኙ ህጻናት ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት የሚሰጠው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዞናዊ የማስጀመሪያ መርሃግብር በቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ በሚገኘዉ በጆሬ ሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ቅጥር ግቢ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤል እንደገለፁት ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በክትባት መከላከል የምንችላቸውንና እንዲሁም ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር እንደ ሀገርም እንደ ክልል በተሰሩ ተግባራት በርካታ የሆኑ አመርቂ ዉጤቶች በመመዝገባቸው የተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫናን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

አቶ ሀብቴ አክለውም በጤናዉ ሴክተር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል በዋናነት የእናቶችና ህጻናትን ጤና ማሻሻል ሲሆን በየደረጃው እየተሰሩ በሚገኙ ተግባራት የእናቶች ህጻናት ሞትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉንና እናቶችንና ህጻናትን ትኩረት ያደረጉ የጤና አገልግሎቶች ሽፋንና ተደራሽነትን ከማሳደግ አንጻር አመርቂ ለዉጦች እየተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክረው የሚሰሩ መሆናቸውን ገልፀው በዛሬው ዕለት የሚጀመረው የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በሀገራችን ለበርካታ ህጻናት ህመም፣ጉዳትና ሞት የሚያስከትለዉን የኩፍኝ በሽታ መከላከል የሚያስችል ትልቅ አቅምና ተግባር በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ9-59 ወራት መካከል ለሚገኙ ሁሉም ህጻናት ጥራቱን የጠበቀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ተደራሽ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ራመቶ አቦ በበኩላቸው የኩፍኝ በሽታ ለህፃናት ህመምና ሞት ምክንያት ከሆኑት በሽታዎች አንዱ መሆኑን በመግለፅ ህፃናትን ከበሽታው መታደግ የሚቻለው በመደበኛና በዘመቻ መልክ በሚሰጠው ክትባት በመሆኑ ህፃናት ከዚህ በፊት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻው እንዲከተቡ በማድረግ ማህበረሰቡ የወላጅነት/የአሳዳጊነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ራመቶ አያይዘውም በዚህ ዘመቻ የተቀናጁ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ፣ የስርዓተ-ምግብ ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ-ጠብታ መስጠት፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድሓኒት መስጠት፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸው እናቶች ልየታና ወደ ጤና ተቋም መላክ እና መሰል የክትባት አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ጠቁመው ለትግበራው ስኬት በየደረጃው ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዛሬ ከግንቦት 6/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በሚሰጠው የተቀናጀ ኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በዞኑ ዉስጥ ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆናቸዉ በአጠቃላይ ከ154 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህፃናት የዘመቻው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመርሃግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤልን፣የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ራመቶ አቦንና የቀዲዳ ገሜላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ክብርት ወ/ሮ ዉባአየሁ በቀለን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮና የዞኑ ጤና መምሪያ ባለሙያዎች፣ የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል።