
ሆሳዕና፦ጥር 10/2018
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በጤናው የበለጸገ ማህበረሰብ ለመገንባት በየደረጃው የተያዙት ዕቅዶች በትክክል ተግባራዊ እንዲሆኑ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በተነቃቃ መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳሰበ።
ቢሮው በወራቤ ዩኒቨርስቲ “ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ቃል ለሰባት ቀናት ለጤናው ዘርፍ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
በአቅም ግንባታ ስልጠናው ማጠቃለያ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አገር ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ህዝብና አቅም እንዳለው አብራርተዋል።
በክልሉ በጤናው ዘርፍ ለአገር ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች ለመስራት እንደሚሰራም ገልጸው፣የጤና አመራሩ የተሰጠውን ስልጠና ወደውስጥ በማስገባት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንዲረባረብም መመሪያ ሰጥተዋል።
አገር የምትጠይቀው የምንችለውን እንድንሰራ ስለመሆኑ ያብራሩት አቶ ሳሙኤል፣የአቅም ግንባታ ስልጠናውን የወሰዱ የዘርፉ አመራሮች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩም አሳስበዋል።
ጠንካራ የጤና ስርዓት በክልሉ እየተዘረጋ እንደሚገኝም ቢሮ ሃላፊው ገልጸው፣በአዲስ መንፈስ በመንቀሳቀስ በጤናው ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀስ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአገራችንም ሆነ የክልላችን ብልጽግና በማይቀለበስ ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያረጋገጡት አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ፣የጤናው ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና በቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የጤናውን ዘርፍ ለማሻገር የተለያዩ ቴክኒክና ታክቲክ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበው፣አመራሩም ሆነ ባለሙያው ለምንድነው የምሰራው?ለማነው የምሰራው የሚለውን በአግባቡ ተገንዝቦ መረባረብ እንዳለበትም መመሪያ ሰጥተዋል።
በአቅም ግንባታ ማጠቃለያው የቢሮው ምክትል ሃላፊዎች፣የማናጅመንት አካላትና የጤናው ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።
በማጠቃለያው ለተለያዩ መዋቅሮች የዕውቅና ሰርተፊኬት የተሰጠ ሲሆን ለሰልጣኝ አመራሮችም ዕውቅና ተሰጥቷል።

