
(ሆሳዕና፣ሰኔ 27/2017)የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አመታዊ ስራ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ እየተካሔደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ አለሙ እንደገለጹት የጤና ቁጥጥር ስራ ዋነኛ አላማ ህብረተሰቡ በጤናው መስክ የሚያገኛቸው አገልግሎቶች ጥራታቸው እና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን እና የተቀመጠላቸውን ደረጃ እንዲያሟሉ መቆጣጠር እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንዲኖር ማስቻል ነው ብለዋል።
የጤናው ስርዓት እንዲጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች በአለም አቀፍ ደረጃ የተነደፉ ኢኒሼቲቮች እንዲተገበሩ ፣በጤናው ስርዓት ውስጥ ያሉ ጉድለቶች መሻሻል እንዲችሉ ታሳቢ ያደረገ ስርዓት መዘርጋቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከቁጥጥር ባለፈ የጤና ስርዓቱን ማገዝ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በጤናው ዘርፍ ብቃት ጥራት እና ደህንነት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ የጤና ባለሙያዎች ሚና የላቀ ነው ያሉት አቶ ፋሲካ በበጀት ዓመቱ ከ3ሺ 800 በላይ ባለሙያዎች የሙያ ምዝገባና ፈቃድ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ መደረጉን በአብነት ጠቅሰዋል።
የጤና ተቋማት የወጣላቸውን ዝቅተኛ መስፈርት እያሟሉ ስለመሆኑ ቁጥጥር ማድረግ ሌላኛው የተቋሙ ተልዕኮ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል።
በክልሉ የጤና ተቋማት የወጣላቸውን የግንባታ መስፈርት ማሟላታቸው፣እንዲይዙ የሚጠበቀውን ግብአት ተግባራዊ ማድረግ ስለመቻላቸው፣የሚያስፈልጋቸውን ባለሙያ ስለማሟላታቸው እንዲሁም በተቀመጠላቸው መስፈርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ማረጋገጥ የተቋሙ አብይ ጉዳይ መሆኑን ነው አቶ ፋሲካ በንግግራቸው ያመላከቱት።
በቁጥጥር ወቅት በርካታ ተቋማት የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እየሰጡ ነው ያሉት አቶ ፋሲካ በአንጻሩ ጥቂት የማይባሉ የጤና ተቋማት ደግሞ ከተቀመጠው መስፈርት በታች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ተቋሙ በህግ እንዲያስፈጽም ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ ሲጋራ ማጤስ የተከለከለባቸውን ስፍራዎች ከህግ አስፈጻሚ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ከትምባሆ ጢስ ነጻ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን አቶ ፋሲካ ጠቁመዋል።
ከችግሩ አሳሳቢነት እና ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ ስራ ተሰርቷል ማለት ባያስደፍርም ከትምባሆ ጢስ ነጻ እንዲሆኑ በህግ የተደነገጉ ተቋማት ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በጋራ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል።
በክልሉ በበጀት አመቱ በቁጥጥር ዘርፉ በሁሉም ተልዕኮዎች ውጤታማ ስራ ማከናወን ተችሏል ሲሉም ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል።
በክልሉ ብቃት ያላቸው የቁጥጥር ተቋማት በመፍጠር በሰው ኃይል፣በግብአት ፣በአሰራር ፣በፋይናንስ፣ በአደረጃጀት የበቁና ከሌብነት የጸዱ፣ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚተጉ አካላትን መፍጠር የሚያስችል ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ፣የክልል ፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በተስፋዬ መኮንን
ለተጨማሪ መረጃ