በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የክልሉ ጤና በትኩረት እየሰራ ነው

  • Post last modified:March 3, 2025

“ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ ለብልፅግናችን!” በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ ጤና ቢሮ መካሄድ በጀመረው መርሃ ግብር የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች የዞንና የልዩ ወረዳ ጤና መምሪያ ኃላፊዎችን ጨምሮ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር የጤናውን ሴክተር ተግባር በአግባቡ እንዲሳለጥ እንዲሁም የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስገንዝበዋል።

በክልሉ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ የክልሉ ጤና ቢሮ በትኩረት አየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ያለመ መድረክ መሆኑን አቶ አሸናፊ አክለዋል።

በክልሉ በዚህ ወቅት ከ1 ሺህ 100 በላይ የጤና ኬላዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ተከትሎ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

የእናቶችና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ፣ የአካባቢን ጤና ከመጠበቅና የቲቢ በሽታን ከመከላከል አኳያ ስኬቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም በዚህ ወቅት በተለያየ ምክንያት የተስተዋለውን መቀዛቀዝ ለማጠናከር የንቅናቄ መድረኩ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በፕሮግራሙ ትግበራና በማሻሻያ ሰነድ ላይ የቡድን ውይይት እየተደረገ ሲሆን ከውይይቱ መነሻ ቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ