“ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስ የቅደመወሊድ ክትትሎችን መጨመር እና የጤና ተቋማትን ማዘመን ያስፈልጋል “ – የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ

  • Post last modified:February 7, 2025

የእናቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጤና የእቅድ አፈፃፀም “ፈጠራዎችን መተግበር እና ማዝለቅ ለላቀ የእናቶች፣ የህጻናት እና ወጣቶች ጤና “ በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገመገመ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ መድረኩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስ የቅደመወልድ ክትትሎችን መጨመር እና የጤና ተቋማትን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልፀዉ በየደረጃዉ ያለዉ አመራር፣ ጤና በለሙያና የሚመለከተዉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በቅንጅት መስራት አለበት ብለዋል።

በጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት ዶ/ር መቅደስ መሻገር ያልተቻሉ ተግዳሮቶችን በምርምር እና በፈጠራ በመታገዝ ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ መሰረታዊ ትኩረት መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

በአፈጻፀም ግምገማ መድረኩም የተገኙ ዉጤቶችንና ቀሪ ተግባራትን በመለየት በቀጣይነት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ተጨማሪ ጥረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትብብር የመስራት ሁኔታን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያደርሱ ዶ/ር መቅደስ ጥሪ አቅርበዋል።

የእናቶች፣ የህጻናትና ጤና እንድሻሻል ያለመታከት እየሰሩ ያሉትን የጤና ባለሙያዎች በየደረጃዉ ያሉ አመራሮች እንድሁም ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።

እናቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ከህዝባችን ቁጥር ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙ በመሆኑ በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መስራት እና አለመስራት በቤተሰብ ደረጃም ሆነ እንደ አገር የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ገልፀዋል።

ያልተዳረሱ ክትባቶችን ለማዳረስ በዘመቻ መልክ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ደረጀ የጨቅላ ህጻናት ሞት ቁጥር መሻሻል ቢያሳይም በቀጣይ ተጨማሪ ጥረቶች መደረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመረጃ ጥራት በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን የተናገሩት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ አንዳንድ አገልግሎቶች በተለይ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አፈጻፀም በክልሎች መካከል የማይጠበቅ ልዩነት በመኖሩ ጉዳዩ በመድረኩ የውይይት ትኩረት መሆን አለበት ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ እየተደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ ርብርብ በርካታ ተጨባጭ ለውጦችን ያስገኘ ቢሆንም በክልሉ የጨቅላ ህጻናት ሞትን ለመቀነስ፣ የድህረ ወሊድ የእናቶች አገልግሎትን ለማሻሻል እና ክትባት ለማዳረስ ተጨማሪ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ ይጠይቃል ብለዋል።

የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ካውንስል ኃላፊ ወጣት ቶፊቅ እስማኤል ሀኪም እና የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ በመድረኩ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህጻናትና ጨቅላ ሕፃናት ጤና ዙሪያ የተዘጋጁ አራት ሰነዶችም በመድረኩ ላይ ይፋ ተደርገዋል።

በግምገማ መድረኩ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች እና ከሙያ ማህበራት እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

ምንጭ የፌዴራል ጤና ሚኒስተር
የማ/ኢት/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ