የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን እና ወረርሽኞች ለመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ ነው አቶ መሙሽ ሁሴን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

  • Post last modified:August 26, 2025

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተብ ጤና ኢኒስቲትዩት ሳምንታዊ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።

ጠንካራ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ እና የጤና ስርዓቱ የበሽታ ቅኝትና የህብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና አፋጣኝ መልስ ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ናቸው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች እና ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠት የህመም፤ የሞት እና የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳይደርስ ተግባራት በትኩረት አየተከወኑ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ማሙሽ ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ ማበርከት መቻሉንም አስገንዝበዋል።

በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ጠንካራ የጤና ስርዓት መኖሩን የተናገሩት አቶ ማሙሽ የበሽታዎች ቅድመ ዝግጅት፤ ትንተና፤ የቅኝት እና የጤና አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ከማጠናከር አኳያ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡

የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጎልበት እንደሚገባ የገለጹት አቶ ማሙሽ የበሽታ ክስተትን መከላከልና የበሽታ ቅኝት ስርዓት እስከታችኛው የጤና መዋቅር ድረስ በተሻለ መልኩ በማጠናከር የመረጃ ቅብብሎሽን በሁሉም ደረጃ ማዘመን ተገቢ ነው ብለዋል።

ሳምንታዊ የድንገተኛ አደጋዎች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ሳምንት የወባ በሽታ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱንና ሌሎች በሽታዎች የሉበትን ደረጃ የቀረበው ሪፖርት አሳይቷል።

የክረምት ዝናብን ተከትሎ ውኃ ያቆሩና ለወባ አስተላላፊ ትንኞች ምቹ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችን ከማፋሰስና ከማዳፈን አኳያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የአጎበር አጠቃቀም ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት፣ የላብራቶሪ ምርመራ ጥራትን ማስጠበቅ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ መስራት፣ በሚሉና በሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ የጤና ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች አጽንኦት በመስጠት መክረዋል።

በዝናሽ ደለለኝ