
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ከዞንና ከወረዳ ለተዉጣጡ ለዘርፉ አስተባባሪዎችና ለልማት እቅድ ባለሙያዎች e-CHIS ትግበራ ዳሰሳ ዙሪያ የማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤናን ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሀ ለዕመንጎ መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት የማህበረሰቡን የጤና መረጃ ስርዓት በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል ።
በክልሉ ከ6 ዓመታት ጀምሮ የማህበረሰብ የመረጃ ስርዓት (e-CHIS) በተመረጡ በክልሉ ወረዳዎች በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይህን የመረጃ ስርዓት ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ነዉ ብለዋል ።
መረጃን በአግባቡ ተንትኖ ከመጠቀም አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በአግባቡ መለየት ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ ሰልጣኞች በተግባር ልምምድ ወቅት ያገኙት እዉቀትና ክህሎት ወደ ስራ በመቀየር ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆን ይገባል ብለዋል ዳይሬክተሩ ።
እንደ አቶ ፍሰሀ ገለፃ የመረጃ አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመን መረጃን በቴክኖሎጂ በማደራጀት እና የመረጃ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በሀላፊነትና በጥንቃቄ መስራት እንደሚገባም አክለዋል።
ይህ የትግበራ ዳሰሳ በ37 ወረዳዎች ላይ እንደሚተገበርም አቶ ፍሰሐ አስገንዝበዋል ።
እንደ ሀገር መረጃን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በጤናው ዘርፍ ወቅታዊ የጤና መረጃን ለመለዋወጥ የዳሰሳ ስራው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ከመድረኩ የተገለፀ ሲሆን የትግበራ ዳሰሳውን (e-CHIS assessmnt) በአግባቡ ሊተገብሩት እንደሚገባ ተመላክቷል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸዉ የትግበራ ዳሰሳው የመረጃ ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዉ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ሳያባክኑ መረጃን በእጅ ስልካቸው እና በኤሌክትሮኒክስ በመጠቀም በፍጥነት ለመለዋወጥ ያስችለናል ብለዋል።
በሸምሲያ አደም