የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሳምንታዊ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ EOC ግምገማ አካሂዷል

  • Post last modified:August 13, 2025

በክልሉ የወባ ጫናን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎች ላይ ቅኝትና ምላሽ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል ።

የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ሳምንታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሳምንቱ 8242 የወባ ኬዝ ሪፖርት መደረጉንና ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ መቀነሱን መመልከት ተችሏል።

የቢሮው ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከለላዉ አቻምየለህ የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ ባለፈው ሳምንት 8556 የወባ በሽታ መከሰቱን ጠቁመዉ በዚህ ሳምንት 8242 ሰዎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ ሲሆኑ ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር (16 በመቶ) መቀነሱን ተናግረዋል ።

በክልሉ በሳምንቱ የወባ ጫና የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ከምባታ 2092፣ ሀዲያ 1692 ፣ስልጤ 1349 ፣ ጉራጌ1159 ፣ሀላባ 692 መሆኑን በሪፓርቱ ተገልጿል ።

በሳምንቱ 57 ሰዎች በወባ በሽታ በተለያዩ ተቋማት ተኝተው ህክምና እያገኙ ስለመሆናቸው ከመድረኩ ተጠቁሟል።።

በክልሉ በሳምንቱ 337 ህፃናት በምግብ እጥረት የተጎዱ ሲሆን 44 የሚሆኑ ህፃናት ተኝቶ ህክምና እያገኙ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ከለላዉ በሪፖርታቸው ።

የቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን የዚህን ሳምንት ቅኝት ሲያብራሩ የወባ በሽታ ስርጭቱ ከባለፈው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ መቀነሱን ጠቁመዋል

የወባ ጫናን በዘላቂነት ለመቀነስ በተመሳሳይ ጫናዉ በጨመረባቸዉ አካባቢዎች ላይ አመራሩን ወደ ፊት በማምጣት በመናበብ እና ትክክለኛ መረጃዎችን በአግባቡ በመለዋወጥ ከተሰራ ከቁጥር ባለፈ ተጨባጭ ዉጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል አቶ ማሙሽ

አቶ ማሙሽ የበሽታዉን ስርጭት በሚፈለገዉ ደረጃ ለመቀነስ ቀጣይነት ያለው እና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የአሰራር ስርዓትን ዘርግቶ ክትትል የማድረግ፣ ቤት ለቤት ጉብኝትን በማጠናከር፣የአካባቢ ቁጥጥር ስራችንን በማጎልበት፣ የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ ፣የህክምና አሰጣጣችንን በማሳደግ እና መሠል ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የህፃናትን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ በራስ አቅም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና የተመጣጠነ ምግብን ለህፃናት በማዘጋጀት በምግብ አጥረት የሚጎዱ ህፃናትን ቁጥር መቀነስ ይቻላል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በተጨማሪም የሌማት ቱሩፋትን በማጠናከርና የህብረተሰቡ ግንዛቤ በማሳደግ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናትን ለመታደግ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባልም ብለዋል አቶ ማሙሽ።

የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸው በዚህ ሳምንት የወባ በሽታ ጫና መቀነሱን ጠቅሰው የቀነሰበትን ተጨባጭ ምክንያት በመለየትና ግኝቱን መነሻ በማድረግ መከላከልን መሠረት ያደረጉ ስራዎችን በማጠናከር ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችሉ የጎርፍ አደጋን ጨምሮ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ለመግታት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የዉይይቱ ተሳታፊዎች አመላክተዋል ።።

በመድረኩም በክልሉ የወባ ወረርሽኝ እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በሸምሲያ አደም