የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ላብራቶሪ የምርመራ አገልግሎት ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡

  • Post last modified:May 8, 2025

ሚያዝያ /29/2017 ዓ.ም

ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያ የሆነው የሕብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት ላብራቶሪ የምርመራ አገልግሎት ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተከናውኗል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያሰተላለፉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የላብራቶሪ ስራ መጀመር በተለያየ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ወረርሽኞችን በመቆጣጠር የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡፡

የህብረተሰብ ጤና ላብራቶሪዎችን መገንባት እና በቴክኖሎጂ ማዘመን ጥራት ያለው የላብራቶሪ አገ/ት እንዲሰጡ በማድረግ ተደራሽነትን ከማሳደጉም ባሻገር የጤናውን ዘርፍ የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ከማሳካት አኳያ ወሳኝ መሆኑንም ነው አቶ ሳሙኤል የተናገሩት

ጥራት ያለውና ወቅታዊ የላብራቶሪ ምርመራ አገ/ትን በማረጋገጥ የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ስራዎችን መደገፍ ይገባል ያሉት ኃላፊው ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን መስራት የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ህይወት የማዳን ስራዎችን ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ምርመራ በአግባቡ ለማሰራትና የደም ውጤት ለማምጣት በተገልጋዩ ማህበረሰብ ላይ ይደርስ የነበረውን ያላስፈላጊ እንግልት እንደሚያስቀርም ገልጸዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስ ፡ የቲቪ ምርመራ እንዲሁም የሌሎች በሽታዎች ውጤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለየት ለታካሚዎች ተገቢ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚረዳ የገለጹት አቶ ሳሙኤል ላብራቶሪው በሙሉ ዓቅሙ በሁሉም ስፔሻሊቲዎች በፍትሃዊነት አገ/ት እንዲሰጥ ለማስቻል በየደረጃው ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አቶ ማሙሽ ሁሴን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በዛሬው ዕለት የተመረቀው የህ/ብ ጤና ላብራቶሪ ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የጤና አገ/ት በመዘርጋት በክልሉ ፓለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ የበሽታ ሁኔታዎችን ቀድሞ በመተንበይ የመከላከልና የመቀልበሻ አቅጣጫዎችን በመከተል ከዓለም ዓቀፍ የምርምርና ላብራቶሪዎች ጋር በመተባበር ችግሮች በፍጥነት ለይቶ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።

ጥራትና ታማኝነት ያለው የላብራቶሪ ውጤት በወቅቱ የማቅረብ ውጫዊ የላብራቶሪ ጥራት ቁጥጥር አገ/ት በሁሉም የጤና ተቋማት እንዲኖር ማድረግ የላብራቶሪ ምርመራ ጥራትን ማስጠበቅ የህብረተሰብ ጤና ላብራቶሪ ዋነኛ ተግባር መሆኑን አቶ ማሙሽ አቶ ማሙሽ አክለዋል።

ለምርመራ የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩትና ከጤና ልማት አጋር ድርጅቶች መገኘቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ ተጨማሪ የምርመራ ዘርፎችን የያዘና ደረጃውን የጠበቀ የላብራቶሪ ህንጻ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በፕሮግራሙ የማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራ ፣ የኢትዮጽያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሳሮ አብደላን ጨምሮ የፌደራል የክልል የዞን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ፡፡

በዝናሽ ደለለኝ