የቴክኖሎጂ አሰራር ስርዓትን በመከተል ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ተጋላጭነት ስጋትን ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ ፡፡

  • Post last modified:July 9, 2025

ሶስተኛው ዙር የክልሉ ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የ2018 በጀት ዓመት የድንገተኛ ጤና አደጋዎች የተጋላጭነት ስጋት ልየታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሀዲያ ዞን ሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር አስተባባሪዎች ስልጠና በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮ ባስተላለፉት መልዕክት በቴክኖሎጂ የታገዘ የህብረተሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች የተጋላጭነት ስጋት ልየታ ስልጠና የቅድመ ትንበያና የዝግጅት ምዕራፎችን በማሳለጥ መሠረታዊ የጤና ችግሮችን ለመለየት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን በማጠናከር ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ማህበረሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን የጤና ቀውስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በቀላሉ ለመቅረፍ ያግዛልም ብለዋል።

የዜጎችን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ለገሰ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ ከስልጠናው በሚገኘው ዕውቀት በመታገዝ ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ እስከ ምላሽ አሰጣጥ ድረስ የተሳለጠ በማድረግ ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓትን መገንባት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ጥራት ያለው የተናበበና ታማኒነቱ የተረጋገጠ የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱን ወቅቱን በሚመጥንና ዘመኑን በዋጀ መንገድ በማደረጀት የመረጃ ጥራትን ማስጠበቅ እንደሚገባ ያመላከቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ ባህልን ለማዳበር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።

ስልጠናው ለቀጣይ አራት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

በዝናሽ ደለለኝ