የክልሉ መንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

  • Post last modified:May 8, 2025

(ሆሳሳዕና፣ሚያዚያ 28/2017)በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን የተገነቡ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) እንደገለጹት ባለፉት ሰባት ዓመታት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተተገበሩ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዓሕመድ (ዶ/ር) ቆራጥ አመራር ሰጪነት የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ ላደረጉት የላቀ ጥረት ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል።

በክልሉ ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉ የመንግስት ፣የፓርቲ እና የህዝብ የተቀናጀ ጥረት ውጤት ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ግብ አስቀምጦ እየሰራ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በክልሉ 1ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚፈጀው በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት መርሐ ግብር 2ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በክልሉ በሰባት ከተሞች 165 ኪ/ሜ የኮሪደር ልማት እየተካሔደ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም ከ4 እስከ 5 ቢሊየን ብር እንደሚፈጅም ጠቁመዋል።

ክልሉ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተከትሎ በሰባት ከተሞች በ4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የቢሮ ግንባታ እየተካሔደ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሽ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማትን በአግባቡ መጠበቅ እና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

የኢፌዲሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ) ኢንጂነር ) እንደገለጹት የፌደራል መንግስት በሀገሪቱ ፍትሀዊ የልማት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ በመንግስት በጀት አሊያም ከልማት አጋሮች በሚገኝ ድጋፍ ዘርፈ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ 44 የልማት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ በባስኬት ፈንድ፣ በዋን ዋሽ፣በሆርን አፍሪካ እና በሌሎችም ፕሮግራሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በሁሉም ዘርፍ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች 7 ነጥብ 3 ቢሉየን ብር እንደሚገመት ሚኒስትሩ አስረድተዋል።ባለፉት 6 ዓመታት ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም አቅም እየጎለበተ ስለመምጣቱም አመላክተዋል።

የጎርፍ የአደጋ ስጋትን ለመከላከል በክልሉ 73 ኪ.ሜ የወንዝ አመራር ስራ ይጀመራል ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም የ560 ሚሊየን ብር ጨረታ ወጥቶ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ፡-ዛሬ ተመርቀዉ ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች መንግሥት ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያለዉን ተነሳሽነት ያሳየበት ነው፡፡

በዞኑ ከ 4 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ፡ ለምርትና ምርታማነት መጨመር ፡ ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ምረቃ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርም ዶ/ር መሐመድ ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው የልማት ፕሮጀክቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ የቡኢ ከተማ አስተዳደር የንጹህ መጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን እና የወልዲያ የመስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሽ መሆናቸውን አቶ ዳዊት ጠቁመዋል።

የቡኢ ከተማ አስተዳደር የንጹህ መጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን በ210 ሚሊየን ብር መገንባቱን የገለጹት ኃላፊው ከ65ሺ በላይ የከተማውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በዞኑ የወልዲያ የመስኖ አውታር በዘላቂ የልማት ፕሮግራም የበጀት ድጋፍ ከ132 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ብር ወጪ ተደርጎበት ለምረቃ መብቃቱን አቶ ዳዊት አስረድተዋል።

ይህ ፕሮጀክት 300 ሄ/ር መሬት ማልማት የሚያስችለል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው 1000 አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በተስፋዬ መኮንን