የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ይበል የሚያስብል ነው ሲሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ገለጹ!

  • Post last modified:February 7, 2025

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ም/ል ርዕሰ መስተዳድርና የት/ት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ በኢፌድሪ ጤና ሚ/ር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ የተመራ የሚ/ር መስሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አካላት ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌና የማኔጅመንት አካላትና እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናቱና የስራ ኃላፊዎቹ የሆስፒታሉን የስራ ክፍሎች ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ካሊድ ሸረፋ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ዶ/ር ካሊድ ከሆስፒታሉ መቋቋም ታሪካዊ ዳራ ጀምረው የተደረገውን የአገልግሎት ማስፋፊያና የወደፊት ራዕዩን ለጎብኚዎቹ ያብራሩ ሲሆን ጉብኝት የተደረገባቸውን የስራ ክፍሎችም የአገልግሎት አሰጣጥና አቅም አስረድተዋል።

ተቋሙ በህ/ሰብ ከፍተኛ ተሳትፎ መገንባቱን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ ከአካባቢውና አጎራባች ዞኖች ባሻገር ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚመጡ ዜጎች የስፔሻሊቲና የሰብ-ስፔሻሊቲ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ አክለዋል።

ሆስፒታሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱን እያስፋፋ መሆኑንም በማንሳት ማስፋፊያውን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለማኖርም የመንግስትን ድጋፍ እንደሚሹ ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ም/ል ርዕሰ መስተዳድር፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ሆስፒታሉ በከፍተኛ የህክምና መሳሪያዎች በመደራጀት የሚሰጠው አገልግሎት የዜጎችን አላስፈላጊ እንግልት የሚቀንስ መሆኑን ጠቁመው ይህም ከክልሉም አልፎ ለሀገር አቅም መሆኑን በመጥቀስም ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ተቋሙ የቀዶ ህክምና የሚሰጥበት የስራ ባህል ሊበረታታና ለሌሎችም ተሞክሮ መሆን የሚችል መሆኑን ያነሱት የኢፌድሪ ጤና ሚ/ር ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ የአዕምሮ ህክምና ክፍል የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም ወደሌሎች የአካባቢው የህክምና ተቋማት መስፋት ይኖርበታል ብለዋል።

ሆስፒታሉ ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮና አስፋፍቶ እንዲቀጥል በማሳሰብ ለዚህም የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ቃል ገብተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ለሌሎች ጤና ተቋማት የሚያደርገው እገዛ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን በማንሳት ይህንኑ ለማገዝ በቢሮው በኩል የተቻለው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ዘገባው የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነው