የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ ፡፡

  • Post last modified:March 21, 2025

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ተግባሮች ዙሪያ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ገምግሟል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በገመገሙበት ወቅት እንዳሉት የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ የበሽታ መከላከል ሥራዎችን በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ የወባ ስርጭት ለመግታትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መጠነ ሰፊ ተግባሮች መከወኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማሙሽ ሁሴን ናቸው፡፡

የበጋውን ዝናብ ተከትሎ የወባ ስርጭት ሊጨምርባቸው የሚችሉ አከባቢዎችን ትኩረት ያደረገና የወባ ስርጭት ለመግታት የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቧል፡፡

ህዝብን በማሳተፍ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂዎችን በአግባቡ በመተግበር መግታት እንዲሁም የወባ ህመምን መቀነስ እና ሞትን ለማስቀረት ታስቧል፡፡

በሀይማኖት ተቋማት በኩል ዋና ዋና በሆኑ የወባ መተላለፊያ መንገዶችና መከላከያ ዘዴዎች ትምህርት በመስጠት ለቀበሌ አመራሮች በወረዳ ማዕከል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት አብይ ተግባር ይሆናል፡፡

የትምህርት ተቋማትን በመጠቀም የግናዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመተግበር የሀገር ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በመጠቀም የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስልቶች ላይ ለማኅበረሰቡ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ታቅዷል፡፡

በክልል ተደማጭ በሆኑ ሚዲያዎች እና በዋናነት የማኅበረሰብ ሬድዮ በመጠቀም በየአካባቢው ቋንቋ የወባ መከላከልና ቁጥጥር ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ለማሰራጨት ታስቧል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በመጠቀም በቤት ለቤት ጉብኝት ወቅት ትኩሳት ያላበቸው ህሙማን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በማስላክ ተገቢውን ህክምና አገልግሎት እንድያገኙ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

በአብርሃም ሙጎሮ