የጤና ሚኒስቴር 4.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሣሪያዎች ለክልል እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ድጋፍ አደረገ

  • Post last modified:August 15, 2025

የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ስርአትን ለማጠናከር የሚያስችል የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ ጤና ሚኒስቴር ለክልል እና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች በዛሬው ዕለት አድርጓል።

የህክምና መሣሪያዎች የህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ያሉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የተደረገው ድጋፍ የጤና ተቋማት የህክምና መሣሪያዎች የረጅም ጊዜ ፍላጎትን የሚያሟላ መሆኑን ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ በመቀጠልም የጤናው ዘርፍ ትልቁ ወጪ የህክምና መሣሪያዎች ግዢ መሆኑን በመግለፅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎቹን በተገቢዉ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲያዉሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው አዲሱ የመድሃኒት ግዢ አዋጅ የተሻለ የህክምና መሣሪያዎች ግዢ ስርዓት እንዲፈጠር በማድረጉ፤ አገልግሎቱ በፍጥነት የህክምና መሣሪያዎች ማቅረብ እንዲችል አድርጎታል ብለዋል።

በድጋፉም ለ48 የጤና ጣቢያዎች ሙሉ ኪት፣ ለ162 አጠቃላይ (comprehensive) ጤና ኬላዎች ኪት፣ ለ50 መሰረታዊ (basic) ጤና ኬላዎች ግብዓት፣ ለ14 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጫ ሙሉ መሳሪያዎች(ኪት)፣ ለ60 የፅኑ ህክምና ማዕከል ግብዓት፣ 33 ዲጂታል X-Ray መሳሪያዎች፣ 19 የላውንደሪ ማሽን፣ 117 የአይን የህክምና መሳሪያዎች (Ophthalmometer) እና ከ3000 በላይ የደም ግፊት መመርመሪያ መሳሪያዎች ተካተዋል።

የክፍፍል ስርዓቱም በፍትሀዊነት ሁሉንም አካባቢ ተጠቃሚ እንዲያደርግ የታሰበ ሲሆን፣ ድጋፉን የክልል እና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ተረክበዋል።

Minstry of health