የጤና ስርዓት አቅም ግንባታ እና ቁጥጥር ፕሮግራም እንዲሁም የጤና መሰረተ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተፈጸሙ ስለመሆናቸው የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

  • Post last modified:August 13, 2025

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ሀብት ልማት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድአሚን በደዊ በ2017 በጀት ዓመት ለነባርና ለአዲስ ፕጀክቶችና ለጤና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ የሚሆን 221,214,255.00 (ሁለት መቶ ሃያ አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ አስራ አራት ሺ ሁለት መቶ ሃምሳ አምስት ብር) ከክልል መንግስት መመደቡን ገልጸው በበጀት ዓመቱ አዲስ ለሚገነቡ ሁሉን አቀፍ ጤና ኬላዎች ግንባታ ለማስጀመር ብር 20,000,000 በጀት ተመድቦ የሁሉ አቀፍ ጤና ኬላ ግንባታ በዞን/በል/ወረዳ ደረጃ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ በጀት ይዘው ግንባታውን ለጀመሩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በድጋፍ መልክ መተላለፉን አስረድተዋል፡፡

በ2017 ዓ/ም ነባር ፕሮጀክቶች 34 ሲሆኑ 5 ፋርማሲ ብሎክ፣ 3 የቀዶ ጥገና ብሎክ፣ 6 የባለሙያ ማደሪያ ግንባታ፣ 11 የጤና አጠባበቅ ማስፋፊያ፣ 2 2ኛ ትውልድ ጤና ኬላ፣ 4 የመጀመሪያ ጀረጃ ሆስፒታሎች እና 3 አጠቃላይ ሆስፒታሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው ከሶስቱ አጠቃላይ ሆስፒታሎች ወልቂጤ አጠቃላይ ሆስፒታል አዲስ ሙሉ ግንባታ ሲሆን ዶ/ር ቦጋለች መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 7 የአዲስ አጠቃላይ /ኮምፕርሄንሲቭ ጤና ኬላዎችን ግንባታ ለማስጀመር ታቅዶ በህብረተሰቡ ንቅናቄ 17 መጀመሩን ያመላከቱት አቶ መሀመድ አሚን በበጀት ዓመቱ ከታቀደው ከ200% በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የ25 የአዲስ መሰረታዊ ጤና ኬላዎችን ግንባታ በዞኖች እና በልዩ ወረዳዎች ለማስጀመር ታቅዶ በህብረተሰቡ ንቅናቄ የ25 ግንባታና እድሳት መጀመሩንና በበጀት ዓመቱ በህብረተሰብ፣ በአጋር ድርጅቶች እና በባለሀብቶች በተገኘ ከ344,122,992 ብር በላይ ድጋፍ ከ97 በላይ የተለያዩ የጤና ተቋማት የግንባታ ፕሮጀክች ግንባታ መጀመሩንና የአብዛኛዎቹ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ መሆኑን አቶ መሀመድአሚን አክለዋል።

የተቀናጀ የስው ሀብት መረጃ ስርዓት ለiHRIS 200 ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ 108 (71.5%) ማሰልጠን መቻሉንም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ውስጥ የተገልጋይ እርካታ መረጃ በመተንተን 3.31 ደረጃ (80%-89%) ማሳካት መቻሉን የጠቀሱት አቶ መሀመድአሚን ለ08 ሲፒዲ ማዕከላት ሁለት ዙር ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ታቅዶ አንድ ጊዜ የድጋፍ ክትትል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የታዩ አበረታች ውጤቶችን በማስጠበቅ በ2018 በጀት ዓመት በእቅድ የተያዙ ተግባራትን በተሻለ ደረጀ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

በዝናሽ ደለለኝ