የ2017 ዓ.ም የጤና ቁጥጥር ስራዎች አፈጻጸም አበረታች ውጤቶች የታዩበት ዓመት እንደነበር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

  • Post last modified:August 13, 2025

በክልሉ ጤና ቢሮ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ አለሙ የባሉሙያ የሙያ ፈቃድ አሰጣጥን በማዘመን (Online) በማስጀመር ለጤና ባለሙያዎች የሙያ ምዝገባ ፍቃድ አዲስ መስጠትና ነባር ማደስ፣የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አዲስ የብቃት ማረጋገጫ መስጠትና ማደስ፣የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥጥር የማድረግ፣ለባህል ህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአሰራር ስርዓት የማበጀት፣የጤና ባለሙያ የሙያ ፈቃድ ሁኔታን በተቋማት የማረጋገጥ (Licensing Status Verification)፣ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅትን የማጠናከር ስራዎች በሰፊው መሠራታቸውን ገልጸዋል።

የ2017 ዓ.ም የቁጥጥሩ ዘርፍ ዕቅድ ዝግጅትን በሚመለከት የ2016 አፈጻጸምን መሰረት ያደረገ የ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ እቅድ እንዲዘጋጅ መደረጉን የጠቆሙት አቶ ፋሲካ የዕቅድ ዝግጅቱ ላይ በየመዋቅሩ ከሚገኙ የቁጥጥር ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር ዕቅዱን የጋራ በማድረግ በቁጥጥር ዘርፉ ላሉ 326 ዳይሬክተሮችና ፈጻሚዎች የሙያ ምዝገባ ፍቃድ አሰጣጥ ላይ፣የቁጥጥር ፓኬጅ ላይ ያተኮረ፣ በጤናና ጤና ነክ ተቋማት ስታንዳርድና መመሪያ ላይ፣ የስንዴ ዱቄት ማበልጸግ ፣በself regulation፣MFR ላይ ያተኮረ ፣በቁጥጥር ዘርፍ ክልላዊ አዋጅ ላይ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የፈጻሚ ማዘጋጃ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

የተቋሙን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መነሻ በማድረግ የ2ኛው ግማሽ ዓመት እቅድን በመከለስ በርካታ ተግባራት መፈጸማቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የታችኛውን መዋቅር የሚያበቁ የድጋፍና ክትትል ስራዎች በ2017 በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ሲፈጸም መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ወርሃዊ ዋና ዋና አፈጻጸሞችን በየወሩ በተቋምደረጃና በኬዝ ቲም ደረጃ ግምገማ የማካሄድና ግብረ መልስ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ ሲሰራ መቆየቱንና በቁጥጥር ዘርፉ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ንቅናቄው እንዲወርድ መደረጉን አቶ ፋሲካ አክለዋል፡፡

ጨረራ አመንጪ በሆኑ የህክምና መሳያሪዎች ላይ በ5 መዋቅሮችና ባሉ ጤና ተቋማት ከሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ የቁጥጥር ስራ መሠራቱን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሩ የታዩ ዋና ዋና ጉዳዩች የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች ፈቃድ እና ዕድሳት፣ የጨረራ መከላከያ ቁሶች አጠቃቀም፣ የጨረራ ውስድ መጠን መለኪያ፣ ከጨረራ አመንጪ መሳሪያ የሚወጣ የጨረራ መጠን ያለበትን ደረጃ የማየትና የመቆጣጠር ሥራ መሠራቱን አስገንዝበዋል።

የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር በስፋት የተሰራበት ዓመት እንደነበር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በቁጥጥር ወቅት በተገኙ ግኝቶች መሰረት 1808(ለ71 ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና፣ለ1737 ጤና ነክ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፤ በ623(73 ጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና 550 ጤና ነክ ተቋማት) ለተወሰነ ግዜ የማሸግ፤ በ4 ጤና ተቋማት ላይ ሙሉ ለሙሉ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ በማድረግ እርምጃ መወሰዱንም አንስተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ግምታቸው ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ መድሃኒትና ምግብ ነክ ምርቶች በቁጥጥር ወቅት በህገወጥ መንገድ ለህብረተሰቡ ለሽያጭ ሊቀርቡ ሲሉ ተይዘው የተወረሱ እና እንዲወገዱ መደረጋቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ ተሳትፎ በነበራቸው ግለሰቦችና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የገለጹ ሲሆን ተቋማቱ እያንዳንዳቸው ከ3 ሺ ብር እስከ 60 ሺ ብር እንዲቀጡ ተደርጎ ብር 1,197,500 ለመንግስት ገቢ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በቁጥጥር ዘርፉ የታዩ አበረታች ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ባለስልጣን መ/ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቀጣይ የተጠናከረ ስራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ፋሲካ አመላክተዋል።

በዝናሽ ደለለኝ