
በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ የተመራ ልዑክ ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጉብኝት አድርጓል
ቡድኑ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡኢ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እንዲሁም በሃዲያ ዞን ንግስት ኢሌኒ ሆስፒታል ፣ በክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሆሳዕና ቅርንጫፍ ላብራቶሪ ፣ ሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተገኝቶ ነው ጉብኝት ያደረገው።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በጤና ተቋማቱ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ላቦራቶሪዎች ላይ ጅምር ነገሮች ቢኖሩም በስታንዳርድ መሠረት የላቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማጠናከር ያስፈልጋል።
ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ምላሽ ጊዜ ከላቦራቶሪዎች ጋር በመቀናጀት የተፋጠና አገልግሎት ለመስጠት በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው ዶ/ር ሳሮ የተናገሩት።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው ቢሮው ባለፉት ጊዜያት ፍትሐዊ የሆነ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም የጤና ተቋማት ተደራሽነት አንጻር በክልሉ አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታና የነባሮች ደረጃ ማሻሻል ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት ኃላፊው።
የመድሐኒት አያያዝ ስርዓት ለማሻሻል የተጀመሩ ነገሮች መኖሩን ያነሱት ኃላፊው በጤና ሚኒስቴር በኩል በተዘጋጀው ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሁሉም ጤና ተቋማት ላይ እየተተገበረ ነው ብለዋል አቶ ሳሙኤል።
በክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ላቦራቶሪ ከማደራጀት አንስቶ በማህበረሰብ ጤና ላይ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች ተሰርቷል ያሉት ደግሞ በክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ናቸው።
ተቋማት ላይ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር ስርዓት በመፍጠር የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ አሰራሮች ተዘርግቷል ሲሉም ተደምጠዋል።
የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኞችን መቆጣጠር ጨምሮ ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና የጤና መረጃዎች ማጠናከር ዋና ተልዕኮዎቹ መሆኑ አቶ ማሙሽ አስረድተዋል።
በአብርሃም ሙጎሮ