
መስከረም 24/2018)
”በባለቤትነት ላይ የተመሰረተ እውቅናና ተጠያቂነት ለጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በቡታጅራ ከተማ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው የክልሉ ጤና ቢሮ አመታዊ የጤና ጉባኤ ተጠናቋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሸው ጣሰው (ዶ/ር) እንደተናገሩት ጠንከራ የጤና ተቋማት ለመገንባት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ይገባል።
የጤና ሴክተርን ለማጠናከር የሰለጠነ የሰው ሀይል አደረጃጀትን ማጠናከር ፣ አሰራሮችን ማጎልበት ፣በተቋም ግንባታ ላይ ማተኮር እና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ማዘመን ይገባል ብለዋል።
የጤናውን ስራ በተግባቦት መስራት ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተጠያቂነትን በማስፈን የጤና ባለሙያዎች በስልጠና ማብቃት እንደሚገባም ገልፀዋል።
በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት ሙሉ ጊዜ በማገልገል ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መትጋት ያስፈልጋል ብለው የጤናው ተግባር በውጤት ሊገለጽ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በጤና ተቋማት የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ለቅሞ በመፍታትና በማረም የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ መረባረብ ይገባል ብለው የማህበረሰብ ተሳትፎን በማጠናከር ጽዱ አከባቢን ለመፍጠር መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተግባርን በማጠናከር የአመራር ሚናና ጥበብን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲሰሩም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው በክልሉ በጤናው ዘርፍ በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ የተመዘገበው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የጤናውን ሴክተር የክልሉ መንግስት በቅርበት እየመራ በመሆኑ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለው ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች በተጠያቂነትና ኃላፊነት ተግባራቸውን ሊያከናወኑ ይገባል ብለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያደርጋቸውን ድጋፍና ክትትል ስራን አጠናክሮ እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እውቅናና ተጠያቂነት ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀው
በበጀት ዓመቱ በጤናው ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች ተሰርቷል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት፣በህፃናት ጤና ክትባት፣ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር፣በህክምና አገልግሎት፣ የጤና ቁጥጥር ስርዓት፣ በማህበረሰ አቀፍ መድኃኒት ቤቶች ግንባታና አገልግሎት ብሎም በሌሎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያጎላ ተግባራት መፈጸማቸውንም የቢሮ ኃላፊ ጠቁመዋል።
የጤናውን ዘርፍ ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት ከመስጠት አኳያም የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለው የሴክተሩን ተልዕኮውን ተግባራዊ ለማድረግ በተጠያቂነት እና በእውቀት ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስራት ያስፈልጋል።
ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን የገለፁት አቶ ሳሙኤል በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቀጣይ ለባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው ስልጠና መስጠት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና ፈጠራ ማዕከላትን መገንባት፣ ተቋማትን መሰረት ያደረጉ ሀብት ማሰባሰብ እንዲሁም በተጠያቂነትና በቁርጠኝነት የጤናው ተግባራት የሚፈፀም ይሆናል ብለዋል።
የጉባኤ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ግንዛቤ በማሳደግ አመርቂ ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልፀዋል።
የጤና ተቋማትን የቅርብ ክትትል በማድረግ በዘርፉ የሚጨበጥ ተግባር ማምጣት መቻሉን ገልፀው የጤና ስራ ለሁሉም ተግባር መነሻ በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመጨረሻም ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እውቅናና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በመድረኩም የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።