
በማእከላዊ ኢትዮጵያ የመስክ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ልኡካን ቡድን ከክልሉ ርእስ መስተዳድር ዶ/ር እንደሻው ጣሰው ጋር ተወያይቷል፡፡ ክልሉ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት የሠጠ በመሆኑ እንደ ወባ ያሉ ወረርሽኞችን መከላከል ተችሏል ያሉት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶ/ር እንደሻው ጣሰው፤ ጤና ሚኒስቴር ለክልሉ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በክልሉ 15 የቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ 17 ጤና ጣቢያዎች፣ እና 18 ፋርማሲዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ርእሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ አስፈላግዉ የጤና ግብዓት እንዲሟላና በአጠቃላይ የጤና ስርአትን ከማዘመን አንጻር ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበው ለውጥ በተጨባጭ የሚታይ መሆኑን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የክልሉ አመራር በተለይም የወባ በሽታን መከላከል ላይ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም አሁንም ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን ለመከላከል ከምንግዜውም በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አክለዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ ለመፍታት ክልሉ ትኩረት መስጠት አለበት ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ በክልሉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር ከክልሉ አመራሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ በሆሳዕና ከተማ የሚገኘውን የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ንግስት እሌኒ መሃመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የጎበኘ ሲሆን፤ በሆስፒታሉ እየተሰጠ የሚገኘውን የድንገተኛ፣ ተመላላሽ፣ ሬዲዮሎጂ፣ የካንሰር ህክምና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ጎብኝቷል፡፡ ሆስፒታሉ አሁን ላይ ባደረገው ሪፎርም የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል መቻሉን መመልከታቸውን የልኡካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ ከሆስፒታሉ ሰራተኞች ጋር የፓናል ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ ለሆስፒታሉ የአንድ አምቡላንስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የጤና ሚኒስትር