በጤና ሚኒስትር ሚኒስትር በዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራው ሉዑካን ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማት ጉብኝት አካሂዷል ፡፡

  • Post last modified:March 3, 2025

የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፈበት የልዑካን ቡድን በክልሉ በጉራጌ እና በሀዲያ ዞኖች የሚገኙ ከጤና ኬላ እስከ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመዘዋወር ጉብኝት አድርገዋል ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የሉዑካን ቡድኑን ተቀብለው የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የተከናወኑ ተግባሮችን ዳሰሳ አድርገዋል፡፡

ቡድኑ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ ፣ በግንባታ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ሆስፒታል እንዲሁም በዞኑ ጉመር ወረዳ የጤና ኬላ እና ሞዴል የቤተሰብ መንደር ጉብኝት አድርገዋል ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ልኡካን ቡድን ጉብኝት በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጉብኝት እና ከሆስፒታል ማህበረሰብ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ባደረጋቸው ጉብኝቶች ወቅት በጥንካሬ በለያቸው በቀጣይ ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ጋር በቅንጅት ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን አጋርተዋል ፡፡

በጉብኝታቸው የክልሉ መንግስት የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እንዲሁም ተደራሽነት ለማረጋገጥ በቅንጅት የሰራቸውን ውጤታማ ስራዎች መመልከት መቻላቸውን የጤና ሚኒስትር ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተቋማት ጉብኝታቸው ወቅት አረጋግጠዋል ፡፡

በጤና ተቋማት ግንባታ፣በማህበረሰብ ጤና መድህን እና በሌሎችም የጤና ልማት ስራ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በአብነት በመጥቀስ ገልጸዋል ።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በየደረጃው ያለው መላው አመራር ለጤና ልማት ስራ በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በወልቂጤ ሆስፒታል ግንባታ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ውይይት እና ጥናት በማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩ በሚፈታበት ጉዳዮች ላይ ይሰራል ብለዋል ፡፡

በሀድያ ዞን የሚገኘውን የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ባደረጉት ጉብኝት ሆስፒታሉ ረጅም አመታት ያገለገለ ከህብረተሰቡ እና ከሆስፒታሉ ሰራተኞች በርካታ መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች ለመፍታት በተሰራው ስራ ከፍተኛ መሻሻሎች መኖራቸውን በሆስፒታሉ የተለያዩ የስራ ክፍሎች በመዘዋወር

በጎበኙበት ወቅት ገልጸዋል ፡፡

ሚኒስተር ዶክተር መቅደስ ዳባ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከህክምና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከማህበረሰቡና ከጤና ባለሙያዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ያጠናክራልም ነዉ ያሉት ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የተመራው ልዑክ ያደረገው የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጉብኝት የክልሉ መንግስት ለጤናው ዘርፍ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራቸው ስራዎች ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል ፡፡

ባለፉት ዓመታት በክልሉ በጤናው ዘርፍ በተሰራው ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል የሆኑ ሆስፒታሎችን መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት ግንባታ ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ስለመሆኑም ኃላፊው በአብነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የአጠቃላይ ጤና ኬላ ግንባታ በስፋት መካሔዱን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ይህም የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ከመከላከል ስራ እስከ ህክምና ባለው ሂደት የህብረተሰቡ፣የአመራሩ እና የባለሙያው የተቀናጀ ትብብር እና ጥረት ውጤታማ ስለመሆኑም ኃላፊው አመላክተዋል።

የህክምና ቁሳቁስ ግብአት አቅርቦት ለዘርፉ ስራ በተግዳሮትነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል በተለይ የመድሀኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የክልሉ መንግስት በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት አማካኝነት በህብረተሰብ ተሳትፎ የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶች መገንባት የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት የተጀመረው ስራ የመድሃኒት አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

የጤናውን ዘርፍ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ የህዝቡን የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም ኃላፊው አስረድተዋል።

በጉብኝቱ የጤና ሚኒስትር ዴዕታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ(ዶ/ር ) እና ሌሎች የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ፡፡

የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ