መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገው የጤና ፖሊሲ አክሞ ማዳንን ጨምሮ እየሰራ ነው፦ ዶ/ር መቅደስ ዳባ

  • Post last modified:March 19, 2025

ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከህዝብ ለተጠየቁ ጥያቄዎች ሚኒስትሮች የሚመልሱበትን “እውነት ነው? ሐሰት” የተሰኘ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከህዝብ ለተጠየቁ ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራ የነበረው የጤና ፖሊሲ አክሞ ማዳንን ጨምሮ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

“ኮሌራ አዲስ አበባን ጨምሮ ሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይ ተከስቷል፤ ጉዳዩን ግን መንግሥት ደብቆታል” እውነት ወይስ ሐሰት? በሚል ለቀረበው ጥያቄ፣ ኮሌራ በግልፅ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ቅኝትና ምላሽ ከሚሰጥባቸው እና ከህብረተሰቡ ጋር የመከላከል ሥራ ከሚሰራባቸው በሽታዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሽታው ደብቀን የሚናቀሳቅሰው ሳይሆን ስም ሰጥተን ከህብረተሰቡ ጋር በግልፅ ተነጋግረን አክሞ ማዳን በሚቻልበት ሁኔታ እየሰራን ነው ብለዋል ዶ/ር መቅደስ፡፡

“ብዙ ታካሚዎች ወደ ውጭ እየሄዱ እንዲታከሙ ተደርገዋል” በሚል ለቀረበው ጥያቄ፣ ከመቶ 82% የህክምና አገልግሎት በመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በፊት የነበሩ ተላላፊ በሽታዎች ቀንሰው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጨመር ብሎም የሚያስፈልጋቸው የህክምና አገልግሎት ከፍ ያለ በመሆኑ ብዙዎች ከሀገር ወጥተው የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ፤ ይህን ከማስቀረት አንፃር መጠነ-ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

በአብርሃም ሙጎሮ