
(ሆሳዕና፣ መጋቢት 14/2017 ዓ/ም) የክልሉ ጤና ቢሮ ጤናና ጤና-ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የ2017 በጀት ዓመት የጤና ቁጥጥር ስራ የባለድርሻ አካላት ንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደተናገሩት የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶችን ጥራት ለማረጋገጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በየደረጃው ሊጠናከሩ ይገባል።
ለዚህም ተከታታይና ቀጣይነት ያላቸው የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ስራዎች እንዲጠናከሩ አቶ አንተነህ አሳስበዋል።
የቁጥጥር መዋቅርን በማጠናከር የመከላከል ተግባራትን ከችግሩ ምንጭ መጀመር ይገባልም ብለዋል-ምክትሉ ርዕሰ መስተዳድሩ።
የቁጥጥር ስራው ውጤታማ እንዲሆን ማህበረሰብ አቀፍ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አንተነህ ጉዳዩን በተመለከተ የወጡ ህጎች እንዲከበሩም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው ለጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ቁጥጥር ውጤታማነት የተቆጣጣሪ አካላትን አቅም ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ አለሙ ዜጎች ጤናቸው እንዲጠበቅና አምራች እንዲሆኑ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችን ጥራት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ጥራቱ የተጠበቀና ደህንነቱ የተረጋገጠ የምግብና መድሃኒት ዝውውርና ስርጭት እንዲኖር የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በጤና ቁጥጥር ዘርፍ የወጡ ህጎችን ተፈጻሚ በማድረግ በህገ-ወጥ የመድሃኒትና የምግብ ንግድ የተሰማሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
መረጃው የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ነው ፡፡