በቀቤና ልዩ ወረዳ የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በፍቃዶ ቀበሌ በይፋ ተጀመረ።

  • Post last modified:May 19, 2025

(ወልቂጤ፣ግንቦት 6/2017) የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ከግንቦት 6 እስከ ግንቦት 15 ለተከታታይ አስር ቀናት በልዩ ወረዳው በሚገኙ ሁሉም ቀበሌያት ክትባቱ እንደሚሰጥ የጤና ተቋሙ አስታውቋል።የቀቤና ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልሀይ ኑርሀሰን በፍቃዶ ቀበሌ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋልከዚሁ ጋር የወላድ እናቶች፣ሕጻናት፣የማህጸን ወደ ውጪ መውጣት ፣የፌስቱላ፣የህጻናት፣የነብሰ ጡርና አጥቢ እናቶች የስነ ምግብ እጥረት ልየታ፣የአንጀት ጥገኛ ትላትልና መከላከያ መዳህኒትና ቫይታሚን”A” ጠብታ መስጠት ስራ በስፋት በዘመቻው እንደሚሰራ ተናግረዋል።ኃላፊው አክለው እንደተናገሩት ወላጆች በተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻው የወላጅነት ግዴታቸውን በመወጣት የድርሻቸውን አስተዋጾ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት አቶ አገኘው ጸጋዬ ክትባቱ እንደ ሀገር መደበኛ ክትባት ዝቅተኛ በመሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች ወረርሽኙ እንዲ ጨምር ምክንያት መሆኑን አመላክተዋል።በኩፍኝ ክትባት ዘመቻው ዕድሜያቸው 9 ወር እስከ 5 ዓመት ያሉ ሕጻናት ክትባቱን ጀምረው ያቋረጡና ያልጀመሩ ሕጻናት እንደሚከተቡ ገልጸዋል።ከኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ጋር በተቀናጀ የስነ ምግብ እጥረት ልየታ፣የቫይታሚንና ትላትል መዳኒት፣መደበኛ ክትባት ላይ 1 ዓመት ሆኖአቸው ክትባት ያልጀመሩና ከ1 ዓመት በታች ሆኖ የሚፈለገውን ክትባት ያሎሰዱ ሕጻናት በዚህ ዘመቻ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።ከ5 ዓመት በታች ሆነው የታመሙ ሕጻናት የሚለዩበት፣የአጥቢና ነብሰ ጡር እናቶች የስነ ምግብ እጥረት የሚለይበት፣ከወሊድ ጋር በተገናኘ የሚከሰተውን ፌስቱላ ልየታ በማድረግ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።በፍቃዶ ጤና ኬላ ሕጻናት ልጆቻቸውን ሲያስከትቡ አግኝተን ካነጋገርናቸው እናቶች ውስጥ ወ/ሮ ለኢላ ነጋሽና መዲና በሰጡት አስተያየት የልዩ ወረዳው ጤና ጽ/ቤት በፈጠረላቸው ግንዛቤ ምስጋናቸውን አቅርበዉ ልጆቻቸውን ለመስከተብ መምጣታቸውን ተናግረዋል።በተያያዘም የሴቶች ልማት ህብረትን በመጠቀም በቀበሌ ደረጃ ቅስቀሳ በማድረግ የዘመቻውን የተቀናጁ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።በተመሳሳይም የኒሀ አካዳሚ መ/ርት ባንቻየው ውቡ የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባትን በማስመልከት በአካዳሚው ከጤና ጽ/ቤቱ ባለሙያዎች ጋር ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ገልጸው በዚህም ሕጻናቱ በዛሬው እለት ክትባት መከተብ መቻሉን ተናግረዋል።በስሜነህ ብልጫ