
የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ የሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድ አሠራርና የአደራጃጀት መመሪያዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እና የዞኑ ሆስፒታሎች የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት እቅድ ክንውን አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አካሂዷል።በመድረኩም የሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድ አሠራርና አደራጃጀት መመሪያ ዙሪያ የተዘጋጁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነዶች እንዲሁም በዞኑ የሚገኙ የ4ቱ ሆስፒታሎች የ2017 ዓ.ም የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የጋራ ምክክርና ግምገማ ተደርጓል።መድረኩን የመሩት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አረጋ እሸቱ ባስተላለፉት መልዕክት በዞኑ የሚገኙ የጤና ተቋማት የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እና የሚሰጡትን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ጥራቱን የጠበቀና ፍትሃዊ እንዲሆን ለማስቻል በየተቋማቱ የተቋቋመው የስራ አመራር ቦርድ በየደረጃው ካሉ የጤናዉ ሴክተር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ይበልጥ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ክቡር አቶ አረጋ እሸቱ አክለውም በዞኑ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየትና አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻልና ለማዘመን የሚረዱ አዳዲስ የሆኑ የፈጠራ አሠራሮችን በመተግበር የተገልጋዩን ህብረተሰብ የህክምና አቅርቦት ፍላጎት ማሟላት ይገባል ብለዋል።በመድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ በሀገር ደረጃ እየተተገበረ በሚገኘዉ የጤና ፖሊሲ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋፋት አንጻር አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረው በዞኑ ውስጥ ያሉ ጤና ተቋማት በክልሉ ከሚገኙ ጤና ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻልና የጤና አገልግሎት ጥራቱን ከማሻሻል ረገድ የሚቀሩ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንዲቻል በተለይም በየሆስፒታሉ የተቋቋመው የስራ አመራር ቦርድ ችግሮችን በጥልቀት በማየት እና በጤና ተቋማት የሚተገበሩ እኒሼትቮችን በመረዳት ተቋማቱን በቅርበት መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ራመቶ አቦ በዞኑ ሥር የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የየተቋማቱ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በዞኑ በየደረጃዉ ከሚገኙ የጤናው ሴክተር መዋቀር ጋር በመቀናጀት በየተቋማቱ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የጤና ተቋማቱ ያላቸውን የተለያዩ አቅሞች በመጠቀም፣ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከርና የሀብት አስተዳደር ሥርአቱን በመምራትና የባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በጤናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ መጥቶ ህብረተሰባችን ተጠቃሚ እንዲሆን የጋራ ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።በመጨረሻም ከመድረኩ ተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎችና አስታየቶች ላይ ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በዉይይቱም በቀጣይ በየሆስፒታሎቹ በሚተገበሩ ተግባራትና የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት የጋራ መግባባት ተፈጥሮ መድረኩ ተጠናቋል።በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤል፣የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ አረጋ እሸቱን እና የከምባታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ ስዩምን ጨምሮ የዞኑ አስተባባሪ አካላት፣የ4ቱም ሆስፐታሎች ቦርድ ሰብሳቢዎችና ሥራ አስኪያጆች፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ማናጅመንት አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።