የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን መረጃ በፍጥነትና በተደራጀ መልኩ ለመሰብሰብና ለመተንተን የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት ለመዘርጋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

  • Post last modified:July 13, 2025

የ3ኛ ዙር የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች የተጋላጭነት ልየታ አስመልክቶ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች በሆሳዕና ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕበረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም የህብረተሰባችንን ጤና ለመጠበቅና ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት፣ የሕብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ተግባራት በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ የምላሽ አሰጣጥና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከልል ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የህብረተሰብ ጤና የድንገተኛ አደጋዎች መረጃን ዲጂታላይዝ በማድረግ የPHEM DHIS2 አተገባበር ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ የድንገተኛ ጤና አደጋዎች የተጋላጭነት ልየታ ተግባራትን በማጠናከር ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች እና ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቀድሞ በመለየት ከሰው ሃይል አቅም ግንባታ ጀምሮ የበጀትና የሎጀስቲክ ዝግጅት በማድረግ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች አስተዳደር ስርዓት መገንባት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ስልጠናው ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ቀድሞ ለመለየት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው ያሉት አቶ ወልደሰንበት ይህም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ይህን ስልጠና በመስጠት የመዋቅሮችን አቅም ለማሳደግ እና አስፈላጊ ቁሳቁስ ለማሟላት እየሰራ መሆኑንም አቶ ወልደሰንበት አክለዋል።

የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ተግባራትን በተገቢው ማሳለጥ የጤናውን ዘርፍ ስርዓት ከማጠናከር አኳያ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ወልደሰንበት የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም አመላክተዋል።

በሶስቱ ዙር የሰለጠኑ 66 ባለሙያዎች በተመደቡባቸው መዋቅሮች ሁሉ የPHEM DHIS2 ሪፖርት የማድረግ ስራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ይህም የድንገተኛ አደጋዎችን መረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም በእጅጉ ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል።

የድንገተኛ ጤና አደጋዎች የተጋላጭነት ልየታ ተግባራትን በማጠናከር ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች እና ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቀድሞ በመለየት ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ኃላፊነት የወሰዱት የስልጠናው ተሳታፊዎች ናቸው።

በዝናሽ ደለለኝ