የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ አመታዊ የጤና ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

  • Post last modified:October 3, 2025

ሆሳዕና መስከረም 23/2018 ዓ.ም

“በባለቤትነት ላይ የተመሰረተ እውቅናና ተጠያቂነት ለጠንካራ የጤና ስረዓት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ አመታዊ የጤና ጉባኤ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊነት አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት እንዳሉት :- የሰው ልጅ ጤናው ሲጠበቅ ሁለንተናዊ ምርታማነትን ማረጋገጥ ይቻላል፣ሃገር የተለመችውን ትልም እውን ለማድረግ ትልቅ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሚከውናቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ የጤና ስራ ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል ሁለት ዓመታት በክልላችን ለጤናው ሴክተር ስራዎች ማንሰራራት መሰረት የተጣለበት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል ብለዋል።

ዓመቱን ስንጀምር በሴክተሩ የነበሩ መሰረታዊ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችል በየደረጃው ያለው አመራርና የሴክተሩን ባለሙያ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትን ሊያረጋግጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን በመስራታችን አጠቃላይ የክልሉን የጤና ነባራዊ ሁኔታ ትርጉም ባለው መልኩ በጋራ መቀየር ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎቻችን፣በጤና ተቋማት የሚያገለግሉ ባለሙያዎቻችን በየደረጃው ላሉ የጤናው ሴክተር አመራሮች አንዲሁም የፖለቲካ አመራሩ ድጋፍ እጅግ የላቀ እንደነበረ ተናግረው በራሳቸውና በጤና ቢሮ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

2017 በጀት ዓመት ክልላችን በጤናው ሴክተር ሞዴል የሚያስብሉትን በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየበት ዓመት ነበር ያሉት ኃላፊው በጥቅሉ ከ11 በላይ የንቅናቄ ሰነዶች በማዘጋጀትና በመግባባት ውይይት ተደርጎ እጅግ ጎላ ያሉ ተጨባጭ ውጤት የታየባቸው ሰለመሆኑም ገልጸዋል።

በቀጣይም ይህን ስራ በማጠናከር አሁን እያስመዘገብን ካለው ውጤት በላቀ ደረጃ ለማስመዝገብ ትኩረት አድርገን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በጤናው መስክ የእናቶችና ህጻናት ጤና ሁኔታ ለማሻሻል ሰፊ ስራ በበጀት ዓመቱ ስንሰራ ቆይተናል በተለይም የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ማሻሻል፣እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል ማሻሻል፣የነብሰ ጡር እናቶች ማቆያ ማስፋፋትና ደረጃቸውን ማሻሻል፣ንጽህናው የተጠበቀ የወሊድ አገልግሎት አፈጻጸምን ማሻሻል፣የህጻናት ክትባት ጥራትና ተደራሽነት ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች መስራት በመቻላችን በተጨባጭ ውጤቶች የታየበት እንደሆነ ማየት ችለናል ከዚህ አንጻር ትኩረታችን በያዝነው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

አቶ ሳሙኤል በበጀት ዓመቱ የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ እንዲሁም የመድሃኒትና ህክምና ግብዓት አቅርቦት አንዱ ሲሆን በመንግስት፣በአጋር አካላት፣በማህበረሰብና ባለሃብት ተሳትፎ ከዚህ አንጻር በርካታ የህክምና ግብዓቶች ማሰባሰብና ለተቋማት ተደራሽ ማድረግ የቻልንበት ዓመትም ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

በያተቋማትን የግብዓትና መድሃኒት አቅረትቦት ችግር መፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ሳሙኤል የህብረተሰቡን አገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ የመድሃኒት አቅርቦት ስርዓቱን ማሻሻል ቁልፍ ጉዳይ በማድረግ በክልላችን ፕሬዝዳንት ኢኒሼቲቭ በርካታ ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት በመሆናቸው በዘርፉ ይታይ የነበረውን የአቅርቦት ችግርና የህዝብ እሮሮ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የቻልንበት ዓመት ልንዘናጋ ባይገባም እጅግ የሚያኮራ ተግባር የተፈጸመበት ዓመት ነው ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ በሁሉም ወረዳዎቻችንና ከተሞቻችን ቢያንስ አንዳንድ ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶች በመክፈት ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ እንድታደርጉ በዚሁ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ከዚህ ቀደም ተጀምረው ለበርካታ ዓመታት ሲጓተቱ የነበሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንደ ቢሮ በወሰድነው አቋም ዛሬ ላይ ሁሉም ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈጻጸም ሂደት ላይ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው ትኩረታችን በያዝነው በጀት ዓመት ተጠናቅሮ አብዛኞቹን ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እንዲበቁ በልዩ ትኩረት የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽ ፕራግራማችን ከማነቃቃት በዘለለ ደረጃው እንዲሻሻል በማድረግና ታቅዶ በተሰራው ስራ በተለይም ሁሉአቀፍ ጤና ኬላ ግንባታን ለማስጀመር በተደረገው ጥረት ከእቅዳችን በላይ በመፈጸም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የቻልንበት በመሆኑ ኮርተንባችኋል አጠናክራችሁ ቀጥሉ የክልሉ ጤና ቢሮም ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ምንም እንኳን በዘርፉ በበጀት ዓመቱ ያሳካናቸው በርካታ ተግባራት ቢኖሩም በጤናው መስክ ዛሬም ትኩረት የሚፈልጉ በያዝነው በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥተን መስራት የሚገቡን ጉዳዮች ስለመኖራቸውም አመላክተዋል።

ይህ ጉባዔ ስኬቶቻችንን በወጉ ተማምረንበት ማላቅና ማስቀጠል፤ጉድለቶቻችንን ደግሞ በቅጡ ተረድተን በቀጣይ ማሻሻል የሚያስችል ተግባቦት፣ቁርጠኝነትና ቁጭት የምንፈጥርበት እንዲሁም ቀጣይ ለሚቀመጡ አቅጣጫዎች ባለቤት ሆነን ለማስፈጸም ዝግጁ የምንሆንበት ጉባኤ ይሆናል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደገለፁት የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓትን ለማጠናከር በቢሮው ቀደም ሲል በርካታ ስራዎች መሰራቱን ገልፀዋል።

ተግባራትን በኃላፊነት በመተግበር የጤናውን ስርዓት በማዘመን ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መስራት ያስፈልጋል ብለው በቀጣይደካማና ጠንካራ ጎኖችን በመለየት በጤናው ዘርፍ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የቢሮዉ ከፍተኛ አመራሮች ፤ የዞን ፡ የልዩ ወረዳና የወረዳ ጤና መህሪያ ኃላፊውች ፤ የሆስፒታሎች የጤና ጣቢያዎች ስራ አስኪያጆችና የጤና ኤክስቴንሼን ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡