የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውጤታማ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው እገዛ ይደረጋል አሉ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ!

  • Post last modified:October 6, 2025

የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሁለንተናዊ የጤናና የህክምና አገልግሎት እያደረጋቸው ያሉ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ እንዲጎለብቱ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።

ሚኒስትር ድኤታዋ የሆስፒታሉን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴዎች በመጎብኘት የሆስፒታሉን አጠቃላይ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል።

ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በውይይቱ ማጠቃለያ ባስተላፉት መልዕክት ወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይድ ሆስፒታል እያስመዘገበ ባለው አጠቃላይ የለውጥ ሂደትና በሚሰጣቸው ሁሉአቀፍ አገልግሎቶች መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ በራስ አቅም እና ተነሳሽነት ዘርፈ ብዙ ፕሮግራሞችን እየተገበረ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ሳህረላ ሂደቱ ፍጥነትና ፈጠራ ከሚለው የመንግስት ኢንሼቲቭ የሚጣጣም መልካም ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በሆስፒታሉ የነበሩ በርካታ የውስጥ ጉድለቶችን በራስ አቅም የፈታበት መንገድ ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ትልቅ ውጤት መሆኑን ሚኒስትር ድኤታዋ ገልጸዋል።

በህክምና መሳሪያዎች አያያዝ፣ በፋይናንስ አጠቃቀም፣ በዲጂታላይዜሽን፣ ንጹህ ከባቢ በመፍጠር፣ በሰው ሀይልና ተቋማዊ አደረጃጀት፣ በማህረሰብ ንቅናቄና ተሳትፎ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በአዳዲስ አገልግሎቶች እንዲሁም በሌሎች ቅንጅታዊ ስራዎችና ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት ሆስፒታሉ ለተሞክሮ የሚበቁ ውጤቶች ማስመዝገቡን ወ/ሮ ሳህረላ መስክረዋል።

እነዚህ ሁላቀፍ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት ሚኒስትር ድኤታዋ ሆስፒታሉን የልህቀት ማዕከል በማድረግ ሂደት ሚኒስትር መስሪያቤቱ ሚናውን ይወጣል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክልል ደረጃ የጤና አገልግሎት ማሳለጫና የተሞክሮ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ የሆስፒታሉን ጉድለቶች በመፍታትና ውጤታማ ተሞክሮዎቹን ወደ ሁሉም ተቋማት በማስፋት ለተሻለ ውጤት እንደሚሰራ አቶ ሳሙኤል አንስተዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአስር አመታት እድሜው ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት ማቅረብ መቻሉን አስታውሰዋል።

ሆስፒታሉ በመጣበት ስኬታማ መንገድ ወደ ተሻለ ከፍታ ለመድረስ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ የዞኑ መንግስትና የስራ አመራር ቦርዱ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አቶ ዘይኔ ተናግረዋል።

የዞኑ ህዝብ የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ ካለው ቁርጠኝነት መነሻ በ2017 ብቻ ከ3 መቶ 50 ሚሊየን ብር በላይ በማህበረሰብ ተሳትፎ ለጤና ልማት ስራ መዋሉን አቶ ዘይኔ አስታውቀዋል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ካሊድ ሸረፋ ሆስፒታሉ ያለፉትን ዓመታት ውጤቶች በመገምገምና ጉድለቶችን በመለየት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ የጤናው ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ የጤና ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና አጠቃላዩ ማህበረሰብ እገዛና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር ኻሊድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ወራቤ/ኮ/ስ/ሆ