የክልሉ መንግስት በወሰደው ቆራጥ ውሳኔ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለውጤት ማብቃት ተችሏል:-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

  • Post last modified:December 24, 2025

(ታህሳስ 13/2018 )የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት በሆሳዕና ከተማ አዲስ ባስገነባቸው ህንጻዎች ስራ መጀመሩን በማስመልከት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አባላት ምልከታ አድርገዋል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በወሰደው ቆራጥ ውሳኔ የልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለውጤት ማብቃት ተችሏል ብለዋል።

የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣የቤተ መንግስት እና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በስድስት ወራት ማጠናቀቅ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

ህንጻዎቹን መገንባት የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ በጊዜ ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ከፍተኛ ሀብት ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።

እየናረ ከመጣው የኮንስትራክሽን ወጪ አንጻር ህንጻዎቹን በጊዜ መጀመር በመቻሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በአብነት ጠቅሰዋል።

በቀሪ ጊዜያት በክላስተር ከተሞች እየተገነቡ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማትን ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

የ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማፋጠን መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አባላት ከመደበኛ ስብሰባቸው በተጓዳኝ ነው በዛሬው እለት የልማት ፕሮጀክቶችን የተመለከቱት ፡፡

የክልሉ መ/ኮ/ጉ/ቢሮ