
በሽታውንም ለመከላከል በጤና ሚንስትር በኩል የተለያየ ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከ”ካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ” ጋር በመተባበር ለ7 ተከታታይ ቀናት በዘመቻ መልክ ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች አንዱ ለሆነው ለኦንኮሴርክያስስ በሽታ መከላከያ የማህበረሰብ አቀፍ መድሐኒት ዕደላ በመስጠት ላይ ይገኛል።
በክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የተመራ የድጋፋዊ ክትትል ቡድን በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ዘመቻው ያለበትን ደረጃ ተመልክቶ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፦የክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰቡን ጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእቅድ እየሰራ ነው። በዚህም አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል።
በተያዘው በዚህ ዘመቻም እንደ ክልል 1.32 ሚሊዮን ህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ ታስቧል ሲሉም ተደምጠዋል አቶ አሸናፊ።
አቶ አሸናፊ፦ በዘመቻው ለበሽታው የሚሰጠውን መድሐኒት መውሰድ ያለበት የህብረተሰብ ክፍል እንድወስድ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዘመቻው ጎን ለጎን በቅንጅት በሚሰሩ ሥራዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት መሥራት እንደሚገባም አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ አሳስበዋል።
በወረዳውም ለመድረስ ከታሰበው ከ134 ሺ 5 መቶ 22 ህብረተሰብ ክፍል የእስካሁን አፈጻጸም 117 ሺ 474 (87%) መድረሱም ተመላክቷል።
የሶሮ ወረዳ ምክትል አስተዳዳርና ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲደሞ ዱነዕሎ በበኩላቸው በዘመቻው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ሊያሻሽሉ የምችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። የእስካሁን አፈጻጸምም አበረታች ነው።
ዘመቻው በክልሉ በሀዲያ ዞን፣ ጉራጌ፣ የምና ጠምባሮ ልዩ ወረዳ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን በአጠቃላይ 19 ወረዳዎችን ተደራሽ ያደረገ ነው።
በአብርሃም ሙጎሮ

