በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአመራር ጥበብ ወሳኝ ነው:-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር)

  • Post last modified:January 22, 2026

(ጥር 14/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና መድህን የ2017 የአፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ (ዶ/ር) በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ በሰጡት የስራ መመሪያ እንደገለጹት በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአመራር ጥበብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ውጤታማ ለመሆን ስራን አቀናጅቶ መተግበር ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የሁሉንም አካላት ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

የቤተሰብ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጤናን መጠበቅ፣ በምግብ ራስን መቻል እንዲሁም የትምህርት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተገቢ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቤተሰብ ብልጽግና ሲረጋገጥ የማህበረሰብ ብሎም የሀገር ብልጽግና እውን እንደሚሆን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ውጤታማ እንዲሆን የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በሁሉም አካባቢዎች የጋራ ቋት ማስጀመር ይገባል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢ የመዋጮ ትግበራን ማጠናከር ተገቢ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከህዝብ የሚሰበሰበውን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በሁሉም ዘርፍ የሚያጋጥም ብልሹ አሰራር መፍታት ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

ችግሮችን በሲስተም እየፈቱ መሄድ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የማህበረሰብ አቀፍ መድሀኒት ቤቶችን ተደራሽነት ማስፋት ላይ ሊተኮር ይገባል ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ የስራ ቦርድ በማጠናከር ችግሮችን እየፈቱ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በስራ መመሪያቸው ጠቁመዋል።

በሁሉም አካባቢዎች አማራጭ የማህበረሰብ መድሀኒት ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

መሰረታዊ መድሀኒቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሰራ ስለመሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሁሉንም አካላት ትብብርና ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው በሀገሪቱ 63 ሚሊየን ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሰው ተኮር እሳቤን ያነገበ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በጤናው ዘርፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ውጤታማ ነው ያሉት ዶ/ር ደረጀ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መደረጉንም በአብነት ጠቅሰዋል።

የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለማስቀረት እየተካሔደ ባለው ጥረት የላቀ ውጤት ስለመመዝገቡም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

የጤና ተቋማት ተደራሽነትን በማስፋት ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት መስጠት ተገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ወረርሽኝን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ክልሉ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ዶ/ር ደረጀ ጠቅሰዋል።