
የጨቅላ ህፃናትና የእናቶች ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማጠናከር እና የመረጃ አያያዝን ዲጅታላይዝ ከማድረግ ረገድ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ 206 የጤና ተቋማትን የኮምፒውተር ድጋፍ ተደረገ፡፡
የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ እና የእናቶችን ጤና ከመሻሻል ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም የመረጃ አያያዝን ከማዘመንና ሙሉ በሙሉ ዲጅታላይዝ ከማድረግ ረገድ አሁንም በርካታ ስራዎች እንደሚቀሩ የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለሆስፒታሎቹ የተደረገው ድጋፍ የመረጃ አያያዙንና የሪፖርት ስርዓቱን በየደረጃው በማዘመን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች ወቅታዊ እና ታዓማኒነት ያለው መረጃ ማድረስ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ከጤና አገልግሎት ጥራትና ቀልጣፋነት አንፃር ከንድፈ ኃሳብ ባለፈ ተቋማት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት እና ተግዳሮቶችን በመለየት መደገፍ የፕሮጀክቱ አንዱ አላማ መሆኑን የገለጹት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ኤስ.ኤል.ኤል ፕሮግራም ኃላፊ አቶ አብይ ሰይፉ ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም መጠነኛ የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ስልጠናዎችም ለተመረጡ ተቋማት እየተሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ 412 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን ለተመረጡ 206 ሆስፒታሎች በመደገፍ የኤልክትሮኒክስ የመረጃ አያያዝን ጨምሮ ሌሎች የዲጅታል ጤና ስርዓትን ለማጠናከር የሚውሉ ሲሆኑ የየሆስፒታሉ እና የየክልሉ ጤና ቢሮ ተወካዮች በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል።

