
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት የ10 ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።
ዳይሬክቶሬቱ የጤናና ጤና ነክ ወረርሽኝ ቅኝት ፣ ዝግጁነት እና ምላሽ እና መልሶ ማገገምን ጨምሮ በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ተግባራትን በልዩነት ተገምግሟል ።
የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወ/ሰንበት ሸዋለም በዚህ ጊዜ እንዳሉት፦ የክልሉ ጤና ቢሮ በወሰደው ጠንካራ የድንገተኛ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ሥራ የወረርሽኝ ምላሽ አቅም በማሳደግ ሞትን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል ።
በዚህም ባለፉት ወራት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደር ሥርዓቱን ለማሻሻል በሁሉም ዞኖች በተመረጡ ወረዳዎችና ጤና ተቋማት ድጋፋዊ ክትትል ተደርጓል ሲሉም ተደምጠዋል አቶ ወ/ሰንበት።
ዳይሬክተሩ፦ በወቅቱም መሠረታዊ የ”PHEM” ስልጠና ከሁሉም ወረዳዎች ለ82 ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት መቻሉንም ተናግረዋል።
የአቅም ግንባታ ሥልጠናውም በኮሌራ፣ በኩፍኝ፣ በወባ፣ በኤሌክትሮኒክ “PHEM” በድንገተኛ ጤና ማህበረሰብ ተግባቦት፣ በማርበርግ ዙሪያ ለ1 ሺ 2 መቶ የጤና ጣቢያና ሆስፒታል ባለሙያዎች እንዲሁም 4 መቶ ለሚደርሱ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መስጠት ተችሏል በማለት አብራርተዋል።
የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ሪፖርት ምሉዕነት እና ወቅታዊነት ለማጠናከር 6427 ነጻ የስልክ መስመር ማስጀመር ሥራም ተሰርቷል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
በክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ወንድሙ በበኩላቸው ወራዳዎች የተሳካ የቅኝትና ምላሽ ሥራዎችን ለማከናወን አክሽን ፕላን በማውጣት መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች የተግባቦት ሥራዎችን እና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የሕብረተሰቡን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል እንዲሰሩ አሳስበዋል አቶ ግርማ።
በወቅቱም የዳይሬክቶሬቱ የ10 ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
አብርሃም ሙጎሮ

