ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሁለተኛው መካከለኛው ዘመን የዕድገት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድና በጤና ሴክተር ሪፎርም ላይ የሚደረግ ሀገር አቀፍ ስልጠና መድረክ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው ።

  • Post last modified:June 27, 2026

በሆሳዕና ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው የሁለተኛው መካከለኛው ዘመን የዕድገት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድና በጤና ሴክተር ሪፎርም መድረክ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ተገኝተው ለተሳታፊዎች ማብራሪያ እና ገለጻ አድርገዋል ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፦ በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በእናቶች ጤና፣ በወባ መከላከል፣ የአከባቢ ጤና አጠባበቅ ላይ እና የጤና ተቋማትን ጽዱና ማራኪ ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎች የሚታይ ለውጥ መጥቷል።

አቶ ሳሙኤል፦ በተለይ ፍትሐዊነትና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማዳረስ በጥናት ወደ ሥራ ተገብቶ እስከ ታችኛው ባሉ ጤና መዋቅሮች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማሻሻል ተችሏል።

በዚህም በ2017 ዓ/ም ብቻ 49 አጠቃላይ ጤና ኬላ (Comprehensive Health Post) ግንባታ አስጀምረናል። የማህበረሰብ መድሐኒት ቤት ከ17 ወደ 51 ማሳደግ ችለናል። ከዚህም 39 ሥራ አስጀምረናል።

አልትራሳውንድ ያላቸው ጤና ጣቢዎችን ቁጥር 112 በማድረስ የተሟላ የጤና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መደረጉን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል ።

በክልሉ በተለያዩ መዋቅሮች የጤና ተቋማት ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ ከአጠቃላይ ጤና ኬላ ጀምሮ ሆስፒታሎች እየተገነቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።

አቶ ሳሙኤል፦በዚህ በጀት ዓመት 14 ዲጅታል X-ray እና 15 ሞባይል X-ray በአጠቃለይ 29 X-ray ማሽኖችን በክልሉ ማስራጨት ተችሏል።

እስካሁን ባለው አፈጻጻም 21 OR block ግንባተቸው ተጠናቆና ግብአት ተሟልቶላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

በጤና ሚኒስቴር የሚንስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ወ/ሮ ረሂማ ሽኩር በበኩላቸው ደረጃ ማሳደግ የሚገባቸው የጤና ተቋማት ጥያቄ ተገቢና አንገብጋቢ በመሆኑ ችግሩ በሂደት እንዲፈታ ይሰራል።

የሰው ኃይል ከማሳደግ አኳያ በጤና ሚኒስቴር ደረጃ በልዩ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ችግሩ እየተፈታ ቆይቷል።

የወባ ጫና ከመቀነስ አንጻር እንደሀገር ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ለዚህም አጎበር ሥርጭት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

ተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ የሚከሰተው የመድሐኒት እጥረት ጉዳይ በሂደት የሚፈታ ሲሆን ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ መድሐኒቶችን ለታለመላቸው ዓላማ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።

በአብርሃም ሙጎሮ