
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጤና ጣቢያ ሪፎርም የተዘጋጀ ማስተዋወቂያ መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤል በዚህ ጊዜ እንዳሉት፦ በጤና ጣቢያዎች ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማሳደግ ጥራት ያለው የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ጤና ጣቢያዎች በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚገለገልባቸው የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመሆናቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ይሰራል ነው ያሉት።
አቶ ሀብቴ፦ የክልሉ ጤና ቢሮ በጤና ተቋማት ላይ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ጥራት ለማሳደግ በእቅድ እየተሰራ ነው። እስካሁን በተሰሩ ሥራዎችም ውጤት ተመዝግቧል።
ለዚህም ለጤና ተቋማት እንደ ሀገር እየተቀረጹ የሚወርዱ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በተዋረድ አገልግሎት ላይ እንዲውል በማድረግ ህብረተሰቡ ከጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል ሲሉም ተደምጠዋል አቶ ሀብቴ።
ጤና ጣቢያዎች የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቀመጠላቸውን ስታንዳርድ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ ሀብቴ፦ በክልሉ ውስጥ ካሉት ጤና ጣቢያዎች በ5ቱ የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ደሣለኝ ሽጉጤ የዞኑ ህብረተሰብ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ በመጀመሪያ ጤና ክብካቤ አሃድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
በመድረኩም የክልሉ ጤና ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎችና ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
አብርሃም ሙጎሮ

