በክልሉ በጤናው ዘርፍ ለአገር ተሞክሮ የሚሆኑና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ለመስራት ሰፊ ርብርብ ይደረጋል፦ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ‎

  • Post last modified:January 18, 2026


‎ሆሳዕና፦ጥር 10/2018

‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በጤናው የበለጸገ ማህበረሰብ ለመገንባት በየደረጃው የተያዙት ዕቅዶች በትክክል ተግባራዊ እንዲሆኑ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በተነቃቃ መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳሰበ።

‎ቢሮው በወራቤ ዩኒቨርስቲ “ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ቃል ለሰባት ቀናት ለጤናው ዘርፍ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።

‎በአቅም ግንባታ ስልጠናው ማጠቃለያ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አገር ለጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ህዝብና አቅም እንዳለው አብራርተዋል።

‎በክልሉ በጤናው ዘርፍ ለአገር ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎች ለመስራት እንደሚሰራም ገልጸው፣የጤና አመራሩ የተሰጠውን ስልጠና ወደውስጥ በማስገባት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንዲረባረብም መመሪያ ሰጥተዋል።

‎አገር የምትጠይቀው የምንችለውን እንድንሰራ ስለመሆኑ ያብራሩት አቶ ሳሙኤል፣የአቅም ግንባታ ስልጠናውን የወሰዱ የዘርፉ አመራሮች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩም አሳስበዋል።

‎ጠንካራ የጤና ስርዓት በክልሉ እየተዘረጋ እንደሚገኝም ቢሮ ሃላፊው ገልጸው፣በአዲስ መንፈስ በመንቀሳቀስ በጤናው ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀስ እንደሚገባም አመላክተዋል።

‎የአገራችንም ሆነ የክልላችን ብልጽግና በማይቀለበስ ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያረጋገጡት አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ፣የጤናው ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና በቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

‎የጤናውን ዘርፍ ለማሻገር የተለያዩ ቴክኒክና ታክቲክ መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበው፣አመራሩም ሆነ ባለሙያው ለምንድነው የምሰራው?ለማነው የምሰራው የሚለውን በአግባቡ ተገንዝቦ መረባረብ እንዳለበትም መመሪያ ሰጥተዋል።

‎በአቅም ግንባታ ማጠቃለያው የቢሮው ምክትል ሃላፊዎች፣የማናጅመንት አካላትና የጤናው ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።

‎በማጠቃለያው ለተለያዩ መዋቅሮች የዕውቅና ሰርተፊኬት የተሰጠ ሲሆን ለሰልጣኝ አመራሮችም ዕውቅና ተሰጥቷል።