የክልሉን ህብረተሰብ ከወረርሽኝ እና ከተለያዩ የጤና ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ

  • Post last modified:June 20, 2026

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጤና ተቋማት ስር ላሉ ባለሙያዎች የPHEM-DHIS2 የተግባር ስልጠና በወራቤ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ይገኛል

የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ስልጠናዉን ባስጀመሩበት ወቅት ላይ እንደገለፁት
ክልሉን ከወረርሽኝ እና ከተለያዩ የጤና ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ ስር በርካታ ዉጤታማ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ለወረርሽኝ የማይበገር የጤና ስርዓትን በመዘርጋት ክልሉ የተሞክሮ ማዕከል እየሆነ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ወረርሽኞች ወቅታዊና በተለያየ ስነ ምህዳር የሚከሰቱ በመሆናቸው የወረርሽኝ ስራዎችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የቅድመ መከላከል ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አቶ ማሙሽ አንስተዋል።

በኢንስቲትዩት ደረጃ የወረርሽኝ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የለማ ሶፍት ዌር (DHIS) መዘጋጀቱን የገለፁት ዋና ደይሬክተሩ ሰልጣኞች አጠቃቀሙ ላይ ተገቢዉን ክህሎት መቅሰም እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል

ህብረተሰቡ የእጅ ስልኩን በመጠቀም በየአካባቢው የሚከሰቱ ወረርሺኞችን ሪፖርት እና ጥቆማ የሚያደርጉበት ድህረ ገፅ በቢሮ ደረጃ መልማቱን እና ስራ ላይ መዋሉን ጠቅሰዉ ከDHIS ጋር በመቀናጀት የመረጃ ቅብብሎሽን ለማቀላጠፍና ፈጣን ውሳኔ ለመወሰን ያስችላል።

እንደ ክልል መረጃን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በጤናው ዘርፍ ወቅታዊ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋ መረጃዎች በተመሳሳይ ጊዜ ለመለዋወጥ ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመን ከወረዳ እስከ ፌደራል ባሉ የጤና መዋቅሮች ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ በትክክለኛ ጊዜ መለዋወጥ እንዲቻል በትኩረት እየተሰራ ስለ መሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው ከስልጤ እና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች እና ማረቆ ልዩ ወረዳ ጤና ጣቢያዎች ለመጡ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ አስተባባሪዎች እየተሰጠ ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ከመድረኩ ተገልጿል

በሸምሲያ አደም