
( ጥር 14/2018) ”ጠንካራ የአመራር ግንባታ ለውጤታማ የጤና ስርዓት” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያ ዙር የጤናው ዘርፍ አመራር አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጤና ልማት ስራን በብቃት ለመወጣት በዘርፉ የሰለጠነ አመራርና ባለሙያዎች ያስፈልጋል።
በጤናው ዘርፍ ያሉ አመራሮች ብቁ በመሆን ከስር ያሉ ባለሙያዎችንና ማህበረሰብን በማስተባበር ለዘርፉ ውጤታማነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በጤናው ሴክተር እምርታዊ ለውጥ ለማምጣት የጤና አመራሮችን በስልጠና ማብቃት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በቀጣይ አመራሩ የመረጃ ስርዓትን ማሻሻል፣ ትክክለኛ የመሪነት ሚና መወጣት፣ ለዘርፉ በቂ ሀብት ማሰባሰብ እና ለሎች አረአያ ለመሆን መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደተናገሩት የጤና ብልጽግናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ የአመራር ስርዓቱን በስልጠና ማጠናከርና መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ቀደም ሲል በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የጤናው ዘርፍ አመራር አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል ለተሻለ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጠንካራ አመራር አቅም ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የጤናው ስርዓት ላይ ያጋጠሙ 15 ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚተገበሩ 12 ስትራቴጂክ መፍትሄዎች በመለየት ወደ ስልጠና መገባቱን ገልፀው እነዚህም በሂደት የሚፈቱ ስለመሆናቸው ገልፀዋል።
የአመራር እና የፈፃሚዎች ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ለጤናው ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ የዘርፉ መሪዎች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማሳሰብ በቆይታቸው የሚያገኙት እውቀት ወደ ተግባር ለመቀየር ስልጠናውን በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲከታተሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሀየሶ በበኩላቸው ለጤናው ተቋማት አመራር የሚሰጠው ስልጠና የጤና ተቋማትን በብቃት እና በእውቀት ለመምራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ውጤታማ የጤና ስርዓትን ለመዘርጋት ስልጠናው የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በስልጠናውም የክልል፣ የዞን እና ልዩ ወረዳዎች የጤናው ሴክተር አስፈጻሚዎች እና ፈጻሚዎች የተገኙ ሲሆን ስልጠናውም ከጥር 14 /2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት የሚሰጥ እንደሆነ ተገልፀዋል።

